የሽብር ቡድኑን ጥቃት በመመከት የሀገራችንን ብልጽግና እናረጋግጣለን!

ዲላ ነሐሴ 08/2013 (ኢዜአ) በሽብር ቡድኑ የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ በመመከት የሀገሪቱን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚካሄደው እንቅስቃሴ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ሲሉ የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ገለጹ።
መምህራኑና ሰራተኞቹ ቀደም ሲል የተተከሉ ችግኞች በመንከባከብና ተጨማሪ በመትከል የአረንጓዴ አሻራ ልማት መረሃ ግብር አካሂደዋል።
በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ፤ የተረጋገጠብንን የህልውና አደጋ በመቀልበስ ለሀገራችን ብልጽግና እንተጋለን ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በማንኛውም ሀገራዊ ጥሪ በንቃት በመሳተፍ ግዴታውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
አሸባሪውን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድባቅ ለመምታት መንግስት ላቀረበው ጥሪ ተገቢውን ምላሽ እንሰጣለን ብለዋል።
በተጓዳኝም ልማትን ለማስቀጠል በአረንጓዴ አሻራ ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን ለመትከልና ቀድሞ የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራ እያካሄዱ ነው።
ለመከላከያ ሰራዊት በገንዘብና ዓይነት ድጋፍ እንዲሁም ደም ከመለገስ ባለፈ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተሰማራበት መስክ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራ እንደሚገኝ ዶክተር ችሮታው ገልጸዋል።
የሽብር ቡዱኑን ጥቃት ከመመከት በተጓዳኝ የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚጠበቅብንን እንወጣለን ብለዋል።
በመንግስት የቀረበው ጥሪ በሀገራዊ ጉዳዮች የጋራ አቋም ለመያዝ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሰራተኛ አቶ ወርቃአገኝሁ በፍቃዱ ናቸው።
በሀገራዊ ጥሪው መሰረት አሸባሪውን ለማጥፋት የሚደረገውን ዘመቻ አቅሜ በሚችለው ሁሉ እደግፋለሁ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው መምህር ዶክተር አለማየሁ አካሉ በበኩላቸው፤ ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ በአረንጓዴ አሻራው ልማት እየተሳተፉ መሆኑንም ተናግረዋል።
ለመከላከያ ሰራዊት የገንዝብና ዓይነት ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻውን ለመመከት ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በተደራጀ መልኩ እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ትናንት ባካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ከ2 ሺህ የሚበልጡ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸው ችግኞችን መትከል ተችሏል።