የዲላ ዩኒቨርሲቲ እጽዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዕከሉ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

ዲላ ነሐሴ 9/2013 (ኢዜአ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ በ15 ሚሊዮን ብር ወጪ ያቋቋመው የእጽዋት ጥበቃና ኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።
ማዕከሉ በአገር ደረጃ ለባለድርሻ አካላት የተዋወቀበት መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በመርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኞችን የመትከልና አካባቢን መንከባከብ ባህል እየሆነ መምጣቱ የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነትን ይቀንሳል።
በዚህ ረገድ ዩኒቨርሲቲው የእጽዋት ጥበቃ ኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ከፍቶ ምርምሮችን ማድረግና ለአካባቢ ጥበቃ ጠቃሚ የሆነ ባህልን በሳይንስ ለመደገፍ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ማዕከሉ የጌዴኦን የአካባቢ ጥበቃ ባህል በዓለም ቅርስነት ከማስመዝገብ ባለፈ ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንደሚያስገኝ ተናግረዋል።
ማዕከሉ ከእጽዋት ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ባለፈ ለምርምርና ጥናት ለተግባር ልምምድ እንዲሁም ለኢኮ ቱሪዝም አገልግሎት እንደሚሰጥ የማዕከሉ ዳይሬክተር መምህር ምትኩ ማንዳ ገልጸዋል።
ማዕከሉ በ100 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ በምርምር የተለዩ ከ500 በላይ የእጽዋትዝርያዎችንና የዱር እንስሳት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
በምርምር ከተለዩትም ውስጥ 30 የሚደርሱት በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እጽዋት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይ ማዕከሉ ለመዋቢያ የሚሆኑ ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ ማቀዱንም አስታውቀዋል።
የኢፌዲሪ የአከባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በእውቀት መታገዝ አለበት ብለዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካባቢ ጥበቃ ሥራን የምርምር ሥራቸው በተጓዳኝ መሰል ተቋማትን ማቋቋም እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን፣ ችግኞችም ተተክለዋል።
(የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ENA))