የዲላ ዩኒቨርሲቲ በአመራርና አሰራር ስርዓት ነባራዊ ሁኔታ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ልምድ ልውውጥ አደረገ፡፡

ዲ.ዩ ነሐሴ 25/2013 ዓ.ም (ህ.ግ) ይህ ተቋም የጋራ እንደመሆኑ መልካም ተሞክሮ ካላቸው ተቋማት ልምድ በመቀመር ተቋማችንን ማሸጋገር የአመራሩ ቁርጠኛ ሀሳብ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ወደድንም ጠላንም በአሁኑ ሰዓት አለም በፈጣን ሁኔታ እየተቀየረች ሀገራትና ተቋማት እየተቀየሩ ባሉበት ወቅት ላይ ተቋማችን የለውጥ ምህዋር ውስጥ በመግባት ለውጡን ማፍጠን ግድ ነው ብለውናል፡፡
የበላይ አመራሩና ሠራተኛው የለውጥ መንገዱን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በፊት የሚሰራበትን አሰራር በመቀየር በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር መዘርጋትና ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ በጀትና እስትራቴጂክ ማኔጅመንት ሲነር ዳይሬክተር ረ/ፕሮፌሰር ብርሃኑ መገርሳ በበኩላቸው የዲላ ዩኒቨርሲቲ በራስ ተነሳሽነት የለውጥ መስመር ውስጥ ለመግባት የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እኛጋ መምጣቱ መደሰታቸውን ገልፀው የጅማ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ሰዓት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ለበርካታ ዓመታት ቀዳሚ ሆኖ የቆዬ አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ረ/ፕሮፌሰሩ አክለውም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ወደዚህ ስኬት ሊመጣ የቻለው በርካታ መሰናክሎችን አልፎ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተቃማችንን ልምዶች እንደ መደላድል በመጠቀም በአጭር ጊዜ ወደ ለውጥ ልገባ እንደምችል ተናግረዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊና የኮምቴው ሰብሳቢ አቶ መሳይ ፍቅሩ ይሄን ለውጥ በተፈለገው መንገድ ወደ ተቋማችን ለማምጣት አሁን ላይ እየተከተልን ያለናቸውን አሰራሮች መቀየር ግድ ይላል ብለዋል፡፡
ያልተማከለ አሰራር በመከተል ሊገጥሙን የሚችሉትን ተግዳሮቶች በመለየትና ለተግዳሮቶቹ መፍትሄ በማዘጋጀት ተቋሙን ወደ ለውጥ መስመር ማስገባት የውዴታ ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አስተያየታቸውን ከሰጡን የዩኒቨርሲቲው ሙሁራን መካከል ዶ/ር አለማየሁ አካሉና አቶ ይመኑ ዳካ ተቋማችን ሰፊ ልምድ ካለው አንጋፋ ተቋም ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ መልካም ተሞክሮዎችን በመካፈላቸው መደሰታቸውን ገልፀው ያልተማከለ አሰራር መከተልና ለተግባራዊነቱ መረባረብ ያስገልጋል ብለዋል፡፡