የዲላ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል ከሠላጣኝ ተማሪ ወላጆች ጋር ውይይትና ጉብኝት አደረገ፡፡

ዲ.ዩ ነሐሴ 27/2013 ዓ.ም. (ህ.ግ) ለአንድ ሀገር ዕድገት ሳይንስና ትክኖሎጂ ዋነኛዉ ምሰሶ ነዉ ያሉት አቶ ተካኝ ታደሰ የSTEM ማዕከል ዳይሬክተር ማዕከሉ ለሀገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጠቁ ዜጎችን ለማፍራት የበኩሉን አስተዋዕፆ እያደረገ ባለዉ ጥረት በጌዴኦ ዞን ከሚገኙ 8 ወረዳዎች እና 4 የከተማ አስተዳደሮች የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ ፈጠራ ዝንባሌ÷ በትምህርት ቤታቸው ባላቸው የፈጠራ ክበብ ተሳትፎ እና በሳይንስ እና ትክኖሎጂ ውጤታቸው ተወዳድረው ያሸነፉትን በማዕከሉ በክረምት ለ2 ወር ስልጠና እና ትምህርት እየተሰጠ እንዳለ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
ማዕከሉ ከተመሰረተበት 2005 ዓ.ም ጀምሮ 2517 ተማሪዎችን አሰልጥኖ እና አስተምሮ ያበቃ ሲሆን በስራ ፈጠራም ብቁ ዜጎችን ማፍራቱን አቶ ተካልኝ ተናገረዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም በዚሁ መስክ ሁለት ስራ ፈጣሪዎች በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ተወዳድረዉ ዕዉቅና እንዳገኙ አክለዉ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በቀጣይ የትምህርት ዘመን በቅዳሜ እና እሁድ መርሀ-ግብር 60 ተማሪዎችን ለማሰልጠን እና ለማስተማር ዕቅድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡
አቶ ንፁህ ከበደ የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ተወካይ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው እንደዚህ ዓይነት የተግባር ትምህርት እና ስልጠና ለታዳጊ ተማሪዎች በመስጠቱ ምስጋና አቅርበዉ የሀገራችን ዕድገት እና ብልፅግና የሚረጋገጠዉ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው÷ ወረዳዎች እና ትምህርት ቤቶች ተባብረን በመስራት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የፈጠራ ባህል አድማሱን በማስፋት ወደታች እንዲወርድ በቀጣይ የትምህርት መርሀ-ግብር አበክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡
በውይይቱ እና በጉብኝቱ ከተገኙት የሰልጣኝ ወላጆች መካከል ወ/ሮ ብዙነሽ ደበበ እና አቶ ሳሙኤል ባሪ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ማዕከል አቋቁሞ የዚህን ዓይነት ስራ በመስራቱ መደሰታቸዉን ገልፀዉ ይህ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በመጨረሻም ወላጆች ልጆቻቸዉ የሚማሩበትንና የተግባር ስልጠና የሚወሰዱበትን የተለያዩ ላብራቶሪዎችና የስራ ፈጠራ የሚሰሩበት ቦታዎችን ጎብኝተው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡