ዲላ ዩኒቨርሲቲ የ2013 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መዝጊያ ስነ-ስርዓት አከናወነ፡፡

ዲ.ዩ ጳጉሜ 03/2013 ዓ.ም (ህ.ግ) በቀጣይ ሁለት ዓመታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን እንተክላለን ያሉት በፕሮግራሙ የተገኙት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እንደ ሀገር “ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ቃል በዚህ ዓመት በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የማኖር ፕሮግራም ዩኒቨርሲቲው በንቃት ሲሳተፍ መቆየቱን ገልፀው በዚህም 121 ሺህ ምግብ ነክ ያልሆኑ፣ 100 ቀርከሀ፣ 8040 ምግብ ነክ የሆኑ እና ተቋሙ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት የሚገኘው ምርጥ የቡና ዘር 247 ሺህ በአጠቃላይ ከ376,000 በላይ ችግኞችን በዩኒቨርሲቲው እና አካባቢው መተከሉን ተናግረዋል፡፡

ጌዴኦ እና አካባቢው አረንጓዴ እንደሆነ የሚታወቅ ቢሆንም የበለጠ አልምተን ለሀገራችን አረንጓዴ አሻራ የማኖሩን ስራ በእጅጉ እናግዛለን ያሉት ዶ/ር ችሮታው ለቀጣይ ዓመት የሚተከሉ ችግኞችን የማፍላት ሥራ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አሳውቀዋል፡፡

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምር/ቴክ/ሽግ/ምክ/ፕሬዝዳንት ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ በበኩላቸው ችግኝ ከተተከለ በኋላ በዘላቂነት እንክብካቤ እንደሚያስፈልግ ገልፀው ችግኝ ከማፍላት ጀምሮ እስከ መትከል ያለው ኢንቬስትመንት ከፍተኛ በመሆኑ እያንዳዱ ችግኝ ሊባክን የማይገባው ትልቅ ሀብት እንደሆነ መታሰብ አለበት ብለዋል፡፡ አካባቢያችንንና ሀገራችንን አረንጓዴ የማልበሱ ፋይዳው መጠነ ሰፊ በመሆኑ የተተከሉ ችግኞች ራሳቸውን ችለው የዕለተ ዕለት እንክብካቤ የማይፈልጉበት ደረጃ እስከሚደረሱ ድረስ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊንከባከባቸው ይገባል ሲሉ ዶ/ር አበባየሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በዕለቱም የዩንቨርሲቲው የበላይ አመራሮች እና የግቢው ማህበረሰብ በጋራ በመሆን የተተከሉ ችግኞችን የመኮትኮትና ውሃ የማጠጣት ፕሮግራም ተከናውኗል፡፡