የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተኮር ሬዲዮ ጣቢያ (FM 89.00) የሥራ አመራር ቦርድ የ2013 ዓ.ም የበጀት ዓመት የእቅድ ክንውን ሪፖርት እና የ2014 ዓ.ም ዕቅድ ላይ ውይይት አደረገ::

ዲ.ዩ ነሐሴ 10/2014 ዓ.ም (ህ.ግ) ሬዲዮ ጣቢያው ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ አሁን ላለበት ደረጃ መብቃቱን የገለጹት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የሬዲዮ ጣቢያው የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ችሮታው አየለ ሬዲዮ ጣቢያው ከአማርኛ በተጨማሪ በአካባቢው በሚነገር በጌዴኦኛ ቋንቋ ፕሮግራም ስርጭት እንደሚያደርግ ገልጸው በኦሮሚኛና በሲዳሚኛ ቋንቋዎች የስርጭት ፕሮግራሙን ለማስፋት እየሰራ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲው ያሉት ኮሌጆች፣ የሥራ ክፍሎች እና የምርምር ማዕከላት ሥራቸውን በሬዲዮ ጣቢያው እንዲያስተላልፉ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ለግቢውና ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ይሰራል ያሉት ዶ/ር ችሮታው የህዝብ ፍላጎትን ለማውቅ አስፈላጊ የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ በቀጣይ አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ ብሎም አሁን ያሉትን ፕሮግራሞች የይዘት ማስተካከያዎችን ለማድረግ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
የሬዲዮ ጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ አስናቀ እንድርያስ በበኩላቸው ጣቢያቸው የተለያዩ ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ጥሩ የሚባል ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው በቀጣይ ቦርዱና የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር ትኩረቱን እንዲጨምር እና እገዛውን እንዲያሳድግ ጠይቀው ሬዲዮ ጣብያው የተሻለ እንዲሆን እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ ከተገኙት መካከል የቦርድ አባላት አቶ አብርሃም መኩሪያ እና አቶ አበበ ቢራራ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንደዚህ ዓይነት ሬዲዮ ጣቢያ ከፍቶ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠቱ የሚመሰገን መሆኑን ገልጸው ሬዲዮ ጣቢያው ከዚህ በላይ የበለጠ እንዲያድግና የስርጭት አድማሱን አስፍቶ ተደማጭ ሬዲዮ ጣቢያ እንዲሆን የበኩላቸውን ሀላፊነት እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡