የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ እና ሪፌራል ሆስፒታል ወደ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምርምርና የህክምና ዕቃዎችን ድጋፍ አደረገ።

ዲ.ዩ መስከረም 12 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዪኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል 8 ለሚሆኑ የመንግስት ተቋማት ወደ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የህክምና ዕቃዎችና የቢሮ መገልገያ መሳሪያዎችን ድጋፍ አደረገ።
ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት እና የዪኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅና እና ሪፌራል ሆስፒታል ማኔጅመንት አጥንቶ ባቀረበው ጥናት መሰረት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት በሙሉ ልብ አፅድቆ በዛሬው ቀን እነዚህን ድጋፎች ለባለድርሻ አካላት እንዲሰጥ መወሰኑን ገልጸው ወደፊትም ይህን መሰሉ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር ዳዊት አያይዘውም እነዚህ የህክምና መሳሪያዎች በርካታ ችግር ያላባቸውና በቅርበትም ህክምና ማግኘት ያልቻሉ ጨቅላ ሕጻናቶች ብዙ ርቀት ሳይጓዙ ባሉበት አካባቢ መሰረታዊ ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችሉም እንደሆኑ ተናግረዋል።
ከመንግስት ብቻ በሚጠበቅ እርዳታ ሆስፒታሎችም ሆኑ የመንግስት ተቋማት ራሳቸውን ችለው የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ስለማይችሉ የግድ እርስ በእርስ መያያዝና መደጋገፍ ይኖርብናል ያሉት ዶክተር ሰላማዊት አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ እና ሪፌራል ሆስፒታል ም/ፕሬዝዳንት ከዚህ ቀደም ሪፌራል ሆስፒታሉ በርካታ ከህክምና ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ መቆየቱን ገልጸው በዛሬው ዕለትም በሆስፒታሉ ስር ለሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች በተለይም በዲላ ከተማ ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና የዞኑን ትምህርት መምሪያን ጨምሮ 8 ለሚጠጉ ተቋማት ወደ 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የምርምርና የህክምና ዕቅዎች ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።
ዶ/ር ሰላማዊት አክለውም ሪፌራል ሆስፒታሉ ይህን ድጋፍ ያደረገው ስለተረፈው አልያም ስለበቃው ሳይሆን ካላው ላይ በመደገፍ ተጋግዞ ማደግ እንደሚቻል በማመኑ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይም ቢሳካና እዚህም ያሉ ባለድርሻ አካላት ቢያግዙ ከዞኑ ጤና መምሪያና ከክልሉም ጋር በመተባበር አሁን በስራችን ያሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን ወደ ጀነራል ከፍ ለማድረግ ዕቅድ መኖሩን ተናግረዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በበኩላቸው እነዚህን የምርምርና የህክምና መሳሪያዎችን የወሰዱ ተቋማቶች ወደ አገልግሎቶች ለውጠው ታች ያለውን የአገልግሎት ጥራት በመጨመር የማህበረሰቡን ችግር መቅረፍ እንደሚገባቸው አሳስበው ዲላ ዩኒቨርሲቲም ይህን ተግባር መፈጸሙ የሚያስመሰግነው ተግባር እንደሆነ በመግለጽ ሌሎችም ይህን መሰሉ ተግባር በምሳሌነት ጭምር ሊወስዱት የሚገባ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው ተቋማት መካከል የቀባዶ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ማቴዎስ መልኬ እና የጌዴኦ ዞን ት/መምሪያ ተወካይ ወ/ሮ ሽታዬ ባሊ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ይህን ድጋፍ በማድረጉ መደሰታቸውን ገልጸው ወደፊትም ይህ አይነቱ ድጋፍ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሌሎች አካላት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።