የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለኮቪድ-19 ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶችን Heart to Heart International ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በድጋፍ መልክ አገኘ::

ዲ.ዩ. መስከረም 22 2014 ዓ.ም. የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል በአሜሪካን ሀገር በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከተቋቋመው Heart to Heart International ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ለኮቪድ-19 ሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ የህክምና ግብዓቶችን ድጋፍ እንደተደረገለት የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና ሪፌራል ሆስፒታል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሰላማዊት አየለ ገልጸዋል፡፡
ድጋፍ የተደረጉት ዕቃዎች በገንዘብ ስሰላ 5,030 የአሜሪካን ዶላር ማለትም ብር 231,000 ዋጋ የሚያወጡና የኮቪድ-19 ህክምና ላይ ለምንሰራቸው ስራዎች ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው የህክምና ግብዓቶች መሆናቸውን ዶ/ር ሰላማዊት ተናግረው ለጠቋማችን ተልዕኮ ስኬት ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የሚደረጉ ትብብሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሰላማዊት አክለውም ይህን ድጋፍ ላደረገልን Heart to Heart International እና ድጋፉ ለተቋማችን እንዲደርስ ላደረጉት በተለይም ለህሊና ከበደ፣ ለብሌን ሞልቶታል እና ለቻርለስ ሁግነር እንዲሁም በተቋማችን በኩል ደግሞ ውጭ ካሉት ኢትዮጵያውያን ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ሁሉ ሲያደርግ ለነበረው ዶ/ር ተስፋነው በቀለ በተቋሙ ስም ምስጋና አቅርበዋል፡፡