የዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ3ኛ (PhD) እና የ2ኛ ዲግሪ የአዲስ ስርዓተ ትምህርቶች ግምገማ አውደ- ጥናት አካሄደ።

ዲ.ዩ መስከረም 22 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የስርዓተ ትምህርቶች የውስጥ እና የውጪ ግምገማ አውደ -ጥናት አካሄደ።
ወደ አውደ-ጥናቱ የመጡ እንግዶችና ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአካዳሚክ እና ምርምር ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌትነት መላኩ አውደ-ጥናቱ ለኮሌጁ የመጀመሪያው የሆነውን የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራም በሕብረተሰብ ጤና (PhD in Public Health) እና ለኮሌጁ 5ተኛ የሆነውን የ2ኛ ዲግሪ ፕሮግራም በአካባቢ ጤና (MPH in Environmental Health) ለመክፈት የተደረገ የካሪኩለሞች ግምገማ አውደ ጥናት መሆኑን አስታውቀዋል።
አቶ ጌትነት አክለውም ዲላ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ መጠን የጤናው ዘርፍ ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አንዱ የትኩረት መስክ ስለሆነ ይህን ተልዕኮውን ለማሳካት የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ፕሮግራሞችን በመክፈት፣ የምርምር ስራዎችን በመስራት፣ የመምህራን ልማት እና አቅም ግንባታ ላይ በማተኮር የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸው ይህ ስርዓተ ትምህርት ተቀርፆ፣ ዳብሮ እና ጸድቆ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ ለኮሌጁ፣ ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለሀገራችን የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአውደ ጥናቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ እንግዶች፣ የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊዎች፣ የኮሌጁ አንጋፋ መምህራንና የዩኒቨርሲቲው ማህበረበረሰብ ተሳታፊዎች ሆነዋል።