የኢትዮጰያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ከ140, 000 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ለአካል ጉዳተኞች የትምህርት መርጃ ቁሳቁሰ ድጋፍ አደረገ::

ዲ.ዩ. መስከረም 28/2014 ዓ.ም (ህ.ግ) ድርጅቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአካል ጉዳተኞች ላይ ድጋፍ በማድረግ እየሰራ እንደቆየ ያስታወሱት ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገ/ምክ/ኘሬዝዳንት ለአካል ጉዳተኞች ስልጠናና ድጋፍ ከመስጠት አልፎ ለሌላው ማህበረሰብ በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ ግንዛቤ የማስጨበጡን ስራ በሰፊው መስራቱን ተናግረዋል::
ዶ/ር ዳዊት አክለው ድርጅቱ የተቋማችን አጋር በመሆን በተለይ አካል ጉዳተኞችን በግብዓት በመደገፍ ሰፊ ስራ እየሠራ ነው ብለዋል::
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል /ECDD/ ባለፉት ግዜያት በርካታ ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አባቡ ተሾሜ ይህ አሁን ያገኝነው ድጋፍ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ውጤታማ ከማድረግም በላይ ለማዕከላችን መጠናከር ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል::
የአካቶት ትምህርት ኘሮጀክት ኦፍሰር የሆኑት አቶ ዩሐንሰ ከ2019 ዓ.ም. ጀምሮ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር መስራታቸውን ገልፀው ይህ የ140000 ሺህ ብር በላይ ግብዓት በተለይ ማየት ለተሳናቸው አካል ጉዳተኞች የሚውሉ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶች መሆናቸውን ገልፀዋል:: የዚህ አይነት ድጋፍም ቀጣይነት እንደሚኖራቸው አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል::