በዲላ ዩኒቨርሲቲ የግዥና ንብረት አስተዳደር አሰራርን ለማዘመን ስልጠና ተሰጠ::

ዲ.ዩ. ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም (ሕ.ግ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የግዥ አጽዳቂ ኮሚቴዎችና ከተለያዩ የሥራ ክፍል ለተወጣጡ ባለሙያዎች በመንግስት ግዥ አስተዳደር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡
በስልጠናው ፕሮግራም ላይ የመክፍቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ የተቀላጠፈ አሰራር በተቋም ደረጃ ለማረጋገጥ ስልጠናው በክህሎትና በዕውቀት ደረጃ ግንዛቤ ለማስጨበጥ አሰፈላጊ መሆኑን ገልፀው እንደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የግዥና ንብረት አስተዳደር አሰራር ሥርዓትን ዘመናዊ ለማድረግ ደንቦች፣ ሕጎችንና መመሪያዎች ተከትለን መሥራትና አሰራሩን ቀልጣፋ ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
ስልጠናውን ስሰጡ ካገኘናቸው መካከል የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አማካሪ ወ/ሮ መቅደስ ብርሃኑ እንደገለፁት የስልጠናው አላማ በየደረጃው በግዥ ላይ ሚና ያላቸው አካላት የመንግስት ግዥ ህግ ግንዛቤ እንዲጨብቱ÷ ከኃላፊነታቸው አንጻር የሚኖራቸውን ተጠያቂነት ለማስገንዘብ እና በህደቱም የአሠራር ሥርዓትን ተከትለው እንድፈጽሙ ለማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የግዥና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አባይነህ መልካ በበኩላቸው የስልጠናው አስፈላጊነት በመንግስት ግዥ መመሪያ መሰረት የዕቅድ እና የግዥ ስርዓቱን አውቀው በግልፅ ጨረታ ብቻ እንዲፈጽሙ፣ የንብረት አስተዳደር ሥራን እንዴት መፈፀም እንደሚገባ እና የግዥና ንብረት አስተዳደር አሰራርን በማዘመን የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖር የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ አባይነህ አክለውም ሁሉም የበላይ አመራሮች ወይም መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም በጀት የሚመደብላው አካላት የግዥ ዕቅዳቸውን በወቅቱ እንድያስገቡ እና ክትትል እንዲያደርጉ ስልጠናው እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን ስከታተሉ ያገኘናቸው የግዥ አጽዳቂ ኮሚቴ ሳብሳቢ ዶ/ር አስናቀ ሙሉየ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ኮሌጅ እና ሪፌራል ሆስፒታል ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ጅግሶ፣ የሀሴ-ዴላ ግቢ ማኔጅንግ ዳይረክተር አቶ ታምራት ፍርዴ እና የፋሲሊቲ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ፈይሳ በስልጠናው ዕቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ በእያንዳንዱ የግዥ ሂደት ምን መደረግ እንዳለበት እና በአሰራር ግልጸኝነት ዙሪያ ስለሚሰሩ ሥራዎች ስልጠናው ሰፊ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡