ከጌዴኦ ዞን ከተለያዩ ወረዳዎች ለተወጣጡ እናቶች ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የግንዛቤና የተግባር ስልጠና ተሰጠ።

ዲ.ዩ ህዳር 3 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ስርጸት ዳይሬክቶሬት ጽ/ቤት ከጌዴኦ ዞን ከኮቸሬ፣ ከይርጋጨፌ፣ ከወናጎ እና ከዲላ ዙሪያ ወረዳዎች ለተውጣጡ እናቶች ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ ስልጠና ሰጠ። ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት በሚገኝበት አካባቢ ላይ የሀይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂ ላይ መስራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የተናገሩት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ስርጸት ዳይሬክቶሬት ዶ/ር ሀብታሙ ተመስገን ስልጠናው የኖሮዌይ መንግስት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር ለመስራት በተስማማው መሰረት በትብብር የተዘጋጀ ስልጠና እንደሆነ ገልጸው በስልጠናው ከዚህ ቀደም ማገዶ ቆጣቢ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ፣ በማኅበር ተደራጅተው በመስራት አምርተው የሚሸጡ፣ ባዮጋዝና ሶላር ኢነርጂን የሚጠቀሙ አዲስ እና ነባር ወደ 40 የሚደርሱ እናቶች መሳተፋቸውን ገልጸው በቀጣይ ሌሎች ወረዳዎችንም ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ዶ/ር ሀብታሙ አክለውም የዲላ ዩኒቨርሲቲ የዚህ አይነት የትብብር ስራዎች ላይ በሩን ክፍት አድርጎ በመስራቱ እና ባለሙያዎቹም እንዲህ ያሉ የትብብር ፕሮጀክቶችን ቀርጸው በማምጣት ስራው ለዚህ ደረጃ እንዲደርስ በማስቻላቸው ከዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ኃላፊዎች ጀምሮ ታች እስካሉ የወረዳዎች ባለሙያዎች ድረስ በጋራ ሊመሰገኑ እንደሚገባ ተናግረዋል። የወናጎ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ትግሉ ሐጢሶ በበኩላቸው ስልጠናው ለእናቶች የተሻለ የስራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ የህብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ቀላልና ዘመናዊ እንዲሆን ለማድረግ ሆነ የማገዶ ጭስ በጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከልና እንዲሁም በየጊዜው እየደረሰ ያለውን የደን ውድመት ለመቀነስ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው ዲላ ዩኒቨርሲቲም እንዲህ ያሉ የህብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ የልማት ስራዎችን አብሯቸው በቅርበት እየሰራ በመሆኑ አመስግነው በቀጣይም ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ከጌዴኦ ዞን ኮቸሬ ወረዳ የመጡት ወ/ሮ ጥግነሽ ገዱ እና ከዲላ ዙሪያ የመጡት ወ/ሮ አለሚቱ በቀለ በበኩላቸው በማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ስራ ላይ ስልጠና ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው በተለይ ስራው በቀላሉ ለመስራት የሚቻል ከመሆኑም በላይ በጤና ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ያለው ጠቀሜታም ከፍተኛ በመሆኑ ከስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ እንዳገኙ ተናግረዋል።