ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአካል ጉዳተኝነት እና አካታችነት ላይ አተኩሮ ለአስተዳደር ሰራተኞች ሊሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

ዲ፡ዩ የካቲት 4.2014 ዓ.ም /ህ.ግ/ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክቶሬት እና የኢትዮጲያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማሕበር በጋራ የአካል ጉዳተኞ እና አካታችነት ላይ አተኩረው ሲሰጡት የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተጠናቀቀ። በስልጠናው 30 ካምፓስ ፖሊስ አባላት እና 30 ከተለያዩ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ዘርፍ የተወጣጡ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት ተሳትፈውበታል፡፡
ዶ/ር አባቡ ተሾመ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክተር እንደገለፁት አካል ጉዳተኞች የተመቻቸ ሁኔታ ከተፈጠረላቸው እንደ ማንኛውም ሰው ሰኬታማ ስራዎችን ይከውናሉ።
የስልጠናው ዋና ዓላማ የጊቢው ማሕበረሰብ ስለ አካል ጉዳተኝነት ግንዛቤ እንዲኖረው ማስቻል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በየስራ ሂደቱ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች አገልግሎት ፈልገው ሲመጡ በበጎ እና በቅንነት መንፈስ እንዲያስተናግዷቸው ማስገንዘብ የስልጠናው ትኩረት መሆኑንም አክለው ገልፀዋል፡፡
አቶ ጀማሊዱን ሱቲ በዲላ ዩኖቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የተቋቋመው ፅ/ቤት አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች አዲስ ተመድበው ከመጡ ጀምሮ እስከ ሚመረቁ ድረስ በስልጠና እና በቁስ ድጋፍ እያደረገ እንደሆን ገልፀዋል።
አቶ ጀማሊዱን አክለውም ለግቢው ማሕበረሰብ በአካል ጉዳተኛነት እና አካቶ መማር ገንዛቤ በመስጠት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ስልጠናውን ከተከታተሉት መካከል ወ/ሮ መሰረት ማቲዎስ እና አቶ ፍሬው ዱኳሌ ከስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልፀው ዩኒቨርሲቲው እንደዚህ ዓይነት ስልጠና ማዘጋጀቱ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
የተፈጠረላቸውን ግንዛቤም ወደ ተግባር በመተርጎም አካል ጉዳተኞችን በተሻለ ትኩረት ለማገልገል እንደሚያውሉት ገልፀዋል።