የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከኘላን እና ልማት ሚንስቴር ጋር በመተባበር ለከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በኘሮጀክት ዝግጅት ዙሪያ ስልጠና ሰጠ::

ዲ ዩ የካቲት 05/2014 ዓ ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ጋር በጋራ ለከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ያዘጋጁት የፕሮጀክት ዝግጅት ስልጠና ተጠናቀቀ።
የመንግስት ኘሮጀክቶችን ስርዓት ባለው መልኩ ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር የሚያስችል ግንዛቤ መፍጠርን አላማ ያደረገው ስልጠና ሲካሄድ፣ ማንኛውም ኘሮጀክት የገንዘብ ፍቃድ ከማግኝቱ በፊት ነባራዊ ሁኔታው ተጠንቶ ዝርዝር ጉዳዮች መታየት እንዳለባቸው አፅንኦት ተሰጥቷል።
ኘሮጀክቶች ከመጀመራቸው በፊት እቅድና ሌሎች ተገቢ ጉዳዮች ቅድሚያ መታየት አለባቸው ያሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ፣ የኘላን እና ልማት ሚንስቴር በኘሮጀክት ዝግጅት ዙሪያ ስልጠና መስጠቱም መንግስት ያስቀመጠውን መመሪያና ደንብ ለመተግበር ወሳኝ እንደሆነ አክለው ገልፀዋል።
ዶክተር ችሮታው አክለውም ስልጠናው ኘሮጀክት ለማስፈቀድ እና ያሰብነውን ኘሮጀክት ለማግኝት ወሳኝ ግንዛቤ የፈጠረ ነውም ብለዋል።
በፌደራል መንግስት የኘሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር አዋጅ 1210/2012 ዓ.ም መሰረት የመንግስት ኘሮጀክት ከዝግጅት ጀምሮ ማለፍ ያለባቸው ሂደቶችና መሰረታዊ መርሆች ተቀምጠዋል ያሉት ደግሞ የኘላን እና ልማት ሚንስቴር የልማት ኘሮጀክት ዳይሬክተር አቶ በረከት ተስፍፅዮን ናቸው።
አቶ በረከት አያይዘውም የተቀመጡትን መመሪያና ደንቦች መሰረት አድርገው ኘሮጀክቱን የሚያዘጋጁና የሚፈፂሙ አካላት ጥራት ባለው ደረጃ እንዲያዘጋጁ በማስቻል የመንግሰትን ሀብት ለታለመለት አላማ ማዋል ይገባል ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ኘሮጀክቶችን እያካሄደ እና ሌሎች ተጨማሪዎችንም ለመጀመር የተለያየ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ያሉት አቶ መሳይ ፍቅሩ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፍ በበኩላቸው ወደ ስራ ሊገቡ የተዘጋጁ ኘሮጀክቶች መንግስት የሚፈልገውን ደረጃ ጠብቀው እንዲዘጋጁ ክህሎት የሚያሰጨብጥ ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል። ከሰልጠናው የሚገኘው ግንዛቤም አሁን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እገዛው ቀላል አይሆንም ሲሉ አክለው ገልፀዋል።
ፕሮጀክቶች በእውቀት ላይ ተመስርተው ሲቀረፁና ሲመሩ አላስፈላግ ብክነትንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከላል ፋይዳ እንዳለው በስልጠናው ተነስቷል።
የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ዲን አቶ ሀብታሙ ካሳ እንደተናገሩት በስልጠናው ትልቅ እውቀት እንዳገኙ ገልፀው የዚህ አይነቱ ስልጠና ተጠናክሮ ቢቀጥል ለተቋሙ እገዛው የጎላ ነው ብለዋል።
የዩኒቨርስቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ከተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ጋር ግንኙነት ያለው ስራ የሚሰሩ እንደመሆናቸው መጠን ስልጠናው ለሚመሯቸው ፕሮጀክቶች በጥራት መሰራትና የሀብት ብክነት ቅነሳ ላይ ውጤታማ አመራር እንዲሰጡ ያስችላል ተብሏል።