በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሪፌራል ሆስፒታል አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ማህበረሰብ አቀፍ ወይይት ተካሄደ፡:

ዲ.ዩ፣ የካቲት 6/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሪፌራል ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጥና አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ማህበረሰብ አቀፍ ውይይት ተካሄደ። የሆስፒታሉን አጠቃላይ አመጣጥ፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የተካሄደው ይህ ወይይት በቀጣይ ሊሰሩ የታቀዱ ተግባራትንም ያካተተ ነበር።
በመርሃ ግብሩ ላይ የመወያያ መነሻ ሪፖርት በዩኒቨርሲቲው የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሪፌራል ሆስፒታል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰላማዊት አየለ አማካይኝነት የቀረበ ሲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎች የአዲሱን ሆስፒታል የግንባታ ሂደት ከጎበኙ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።
ዶክተር ሰላማዊት በሪፖርታቸው የሆስፒታሉን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚዳስሱ በርካታ ሀሳቦችን አንሰተዋል። እንደ እርሳቸው ገለፃ በ1977 ዓ.ም. ዲስትሪክት ሆስፒታል ሁኖ ስራ የጀመረው ይህ ተቋም ማስተማሪያና ሪፌራል ሆስፒታል ሆኖ በዩኒቨርስቲው ስር የተዳደረበትን ያለፉትን አመታት አካቶ በአጠቃላይ በውስጡ 42 ስፔሻሊስት ሀኪሞችን እና 67 ጠቅላላ ሀኪሞችን አሁን ላይ ይዟል። እንደ ማስተማሪያ ሆስፒታልነቱም በዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ስር 19 የቅድመ ምረቃ፣ ሶስት የሁለተኛ እና አንድ የሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ከፍቶ በርካታ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራቱ እንደ ጠንካራ ተግባር ተነስቷል።
ሆስፒታሉ ከጌዴኦ ዞን ባለፈም ለአጎራባች የኦሮሚያ እና ሲዳማ ክልሎች ጭምር ሰፊ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ የመፀዳጃ ቤት ግንባታ፣ የአካባቢው ንፅህና አጠባበቅ እና የእናቶች ጤና ግንዛቤ ፈጠራ ዘርፎች ላይ ጥሩ የሚባል የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ምክትል ፕሬዝዳንቷ ዶክተር ሰላማዊት አክለው አንስተዋል። እሳቸው አክለውም ሆስፒታሉ በሀገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ስጋት የሆነውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል በዞኑ ደረጃ ብቸኛ የለይቶ ማቆያ እና ምርመራ ማዕከል በመሆን፣ ለአጎራባች የጤና ተቋማት ባለሙያዎች በሽታውን በመከላከል ዙሪያ የስልጠና እና ግንዛቤ ፈጠራ እድል በማመቻቸት፣ ማህበረሰቡን በተቀናጀ መልኩ በማንቃት እና ልዩ ተጋላጮችን የኮሮና ክትባት እንዲያገኙ በመስራት ረገድ ስኬቶች ተመዝገበዋልም በለዋል-በሪፖርታቸው።
ከኮሮና ባሻገርም በመደበኛ የጤና ህክምና በኩል ሆስፒታሉ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለበርካታ ህሙማን የአጥንት ቀዶ ህክምና አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ይህም የዞኑና አጎራባች ማህበረሰቦች ህክምናውን ለማገኘት ወደ ሌሎች ቦታዎች ይጓዙበት የነበረውን ርቀት በመቀነስ የወጪና የጊዜ ብክነትንን ማስወገድ ችሏል። በቀጣይም ከማህበረሰቡ ሰፊ የጤና ዘርፍ አገልግሎት ፍላጎቶች መጠንከርና ተደራሽነት አናሳነት አንፃር መሰረታዊ የሆኑ እቅዶችን በመንደፍ የሲቲ ስካን ማሽን ተገዝቶ ወደ ስራ የማስገበት እንቅስቃሴ ላይ ነው። በህክምና ረገድ የካንሰር፣ የአንገት በላይ እና የአንጎልና ህብረ-ሰረሰር ቀዶ ህክምናዎችን ለመጀመር ዝግጅት እየደረገ መሆኑን ለውይይት በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።
ይሁንና ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ እና ከዚህ በተሻለ አገልግሎት እንዳይሰጥ በርካታ ተግዳሮቶች ተደቅነውበታል ብለዋል ዶክተር ሰላማዊት። የመድሃኒት እና ላብራቶሪ እቃዎች አቅርቦት ችግር፣ የአዲሱ ሆስፒታል ህንፃ ግንባታ መጓተት ደግሞ ዋነኞቹ ጊዜ የማይሰጡ ችግሮች ተብለው የተለዩት ናቸውም ብለዋል።
በተለይም ከተጀመረ ስምንት ገደማ አመታትን አስቆጥሮ አሁንም ያልተጠናቀቀው እና 600 የህሙማን አልጋዎች፣ አስራ አንድ የቀዶ ህክምና ክፍሎች፣ በአጠቃላይ ደግሞ አንድ ሺህ 500 ክፍሎችን ይዞ እየተገነባ ያለው ግዙፍ የህክምና ህንፃ በተቀመጠለት ጊዜ ያለመጠናቀቁ ጉዳይ ሆስፒታሉ የሪፌራልነትን ደረጃ ከጤና ሚኒስቴር ለጊዜው እንዳያገኝ እንቅፋት ሁኗል ሲሉ ገልፀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የማህበረሰብ ክፍሎችም በሪፖርቱ ላይ ሀሳብ ከማንሳታቸው ቀደም ብሎ ይሄንኑ ግንባታው መጓተቱ የተገለፀውን አዲሱን የህንፃ ግንባታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። በእለቱም የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለን ጨምሮ፣ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ፣ የዲላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የሆስፒታሉ ቦርድ አመራር ሰብሳቢ አቶ ተስፋፅዮን ዲካ እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ከጉብኝቱ መልስም ተወያዮቹ በቀረበው ሪፖርት፣ በሆስፒታሉ አጠቃላይ አሰራር፣ በአዲሱ ህንፃ ግንባታ መጓተትና በቀጣይ የሆስፒታሉ እጣፈንታ ላይ ጥያቄና አስተያየት አንስተዋል። ተሳታፊዎቹም ሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የሀኪሞች ሙያዊ ስነ-ምግባር፣ የመድሃኒት አቅርቦት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የግቢ ንፅህና እና መሰል ጉዳዮች ላይ የሚነሱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡም ለከፍተኛ ችግር እና ምሬት እየተዳረገ ነውም ብለዋል። የአዲሱ ህንፃ ግንባታ ለምን በታቀደለት ጊዜ አላለቀም? የዩኒቨርስቲው እና የከተማው ብሎም የዞኑ አመራር በዚህ ላይ የተቀናጀ አመራርነት ለምን አልሰጡም? የሚሉ ጥያቄዎችም ለአወያዮቹ ተሰንዝረዋል። ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡት ተወያዮች የሆስፒታሉ ጉዳይ በቀላሉ የሚያዩት እንዳልሆነ አንስተው፣ ፈጣን የአመራርነት ስራ ተስርቶ ለማህበረሰቡ በአቅሙ ልክ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉም አንስተዋል።
ከተወያዮቹ ለተነሱት ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ማብራሪያ የሰጡት የዲላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በአንፃሩ በሆስፒታሉ ላይ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መጓተትና የሙያ ስነምግባር ችግሮችን የሆስፒታሉ አመራሮች በአስቸኳይና በትኩረት ፈትሸው እንዲፈቱ አሳስበው፣ ከአቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን በማስረጃ አስደግፈው ለዩኒቨርስቲው የበላይ አመራር እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ሰጥተዋል። በተጨባጭ የሚታዩ እና በማስረጃ ለተደገፉ ጥፋቶች ያለ ማመንታት በትኩረት መፍትሄ እንሰጣለን ያሉት ዶክተር ችሮታው የመድሃኒት እጥረት ላይ የሚነሱትን ጥያቄዎች በተቻለ መጠን ዩኒቨርስቲው ሌሎች ስራዎችንም ቢሆን አጥፎ ከመንግስት የግዥ ስርአት ጋር በማጣጣም ግዥ ለመፈፀምና ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መጥቷል፤ አሁንም ይሰራል ብለዋል።
ከአዲሱ ሆስፒታል የግንባታ መጓተት ጋር በተገናኘ የሚነሳው ችግር ተገቢ ነው ያሉት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ነገር ግን የችግሩ መሰረታዊ ቁልፍ ያለው የግንባታ ተቋራጩ በቶሎ አለማጠናቀቅና አቅም ማነስ ላይ ነው ብለዋል። ከግንባታ ተቋራጩ ጋር ተደጋጋሚ ጊዜ ውይይትና ግምገማ ቢደረግም ለውጥ አልታየም፤ ውሉን አቋርጦ ስራውን ለሌላ ተቋራጭ ለመስጠትም የመንግስት አሰራር ጋር የሚነሱ ሂደቶች ነገሩን አክብደውብናል ብለዋል። ይሁን እንጅ የጉዳዩን አሳሳቢነትና የችግሩን ግዝፈት በመገምገም ወደ ከፍተኛ የመንግስት አካል ጉዳዩ ተወስዶ ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሆነ ያነሱት ዶክተር ችሮታው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም ግንባታውን በአካል መጥቶ እንዲጎበኝና ውሳኔ እንዲሰጥ ተጠይቆ መልስ እየተጠበቀ ነውም ሲሉ አክለዋል::
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው ከኮስፒታሉ የደረጃ አሰጣጥ ጋር የሚነሱ ሀሳቦች መጤን እንዳለባቸው ገልፀው የደረጃ አሰጣጡ የራሱ መለኪያ ያለው በመሆኑ ጤና ተቋሙ አሁን ካለበት የጀነራል ሆስፒታልነት ወደ “ኮምፕርሄንሲቭ” እንዲያድግ የሚጠበቁ መስፈርቶች እንዲሟሉ የሚመለከተው ሁሉ በጋራ ይሰራልም ብለዋል።
ከሆስፒታሉ የግንባታ መጓተት ጋር በተያያዘም ከተለያዩ አካላት ጋር የሚመለከታቸው ሁሉ እንዴት መሩት ብለን ገምግመናል፤ ነገር ግን የተቋራጩ አፈፃፀም መዳከም ትልቁን ድርሻ እንደያዘ ተረድተናል ብለዋል የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ። እንደ አቶ አብዮት ገለፃ ከሆነ በየደረጃው የታዩ ጉድለቶች እንዲፈቱ እና አጠቃላይ የሆስፒታሉ አገልግሎት ማህበረሰቡ በሚፈልገው ልክ የተሻሻለ እና የተቀላጠፈ እንዲሆን መፈታት ያለባቸው በቶሎ ይፈታሉ ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርስቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሪፈራል ሆስፒታል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰላማዊት አየለ በበኩላቸው ከተወያዮቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተው፣ አብዝሃኛዎቹን አስተያየቶችና ቅሬታዎች ጠንክረን ለመፍታት በግብአትነት የሚወሰዱ ናቸው፤ በቀጣይም እንደየ ጉዳዮቹ ክብደት ደረጃ እየለየን እየፈታን ህብረተሰቡን በተሻለ አገልግሎት ለመካስ እንሰራለንም ብለዋል።
የዲላ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባና የሆስፒታሉ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋፅዮን ዳካ በበኩላቸው የግንባታ መጓተቱን ጉዳይ የዩኒቨርስቲው አመራር እና የቦርድ አባላቱም ከዚህ በፊት በጉዳዩ ላይ በተደረጉ ግምገማዎች የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን መሰረት አደርገው በትኩረት እየሰሩበት እንደሆነ ገልፀዋል። ከንቲባው አክለውም ከመልካም አስተዳደርና አገልግልት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ችግሮች የተነሱ በመሆኑ አመራሩ ቅሬታዎቹን ወስዶ በፍጥነት ለመፍታት አቅጣጫ ባስቀመጠው መሰረት ለመስራት ቃል ይገባልም ብለዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ውይይቱ በቀጣይ የተነሱ ጥያቄዎችና ችግሮችን በተጨባጭ ሰርቶ ለውጥ ለማሳየት ቁርጠኛ አቅጣጫ እንዲከተል በመግባባት፣ የአዲሱ ህንፃ ግንባታ መጓተትን ለመቅረፍም ህብረተሰቡ ከመጠየቅ ባለፈ በቅርበት ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያደርግ በመነጋገር ተጠናቋል።