የዲላ ዩኒቨርሲቲ ለምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ከ221 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።

ዲ.ዩ የካቲት 9 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ በመልማት ላይ የሚገኝ የስንዴ እርሻ በስንዴ ዋግ በሽታ በመጠቃቱ ከ221ሺህ ብር በላይ የሚሆን የአይነትና የስልጠና ድጋፍ አደረገ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ክብሩ አለሙ ከዩኒቨርሲቲው የተደረገውን ድጋፍ ባስረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደምም ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር ገልጸው ዛሬ ደግሞ አርሶ አደሩ የስንዴ እርሻው በስንዴ ዋግ በመጠቃቱ የአባያ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ላቀረበው የድጋፍ ጥያቄ አመራሩ ፈጣን ምላሽ በመስጠት በዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር አካውንስል በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ከ221 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ ክብሩ አክለው ቦታው ላይ ከፍተኛ የሆነ የክህሎት ክፍተት ያለ በመሆኑ ችግሩ በባለሙያዎች ጭምር ተጠንቶ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ5 ያላነሱ ባለሙያዎችን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት ሳይንስ ት/ት ክፍል በማወቀር ቦታው ላይ በቂ የሆነ ስልጠና ለባለሙያዎች እንዲሰጥ ጭምር መደረጉንም ተናግረዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የአባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከበደ አሬራ በበኩላቸው ላቀረቡት የድጋፍ ጥያቄ ዩኒቨርሲቲው አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ በማህበረሰቡ ስም ምስጋና አቅርበዋል ።
የአባያ ወረዳ ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አየለ ዋቆም ዩኒቨርሲቲው ለጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ በመስጠት ያደረገው ከፍተኛ ድጋፍ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ሁሌም የሚያስመሰግነው ተግባር እንደሆነ ተናግረው በቀጣይ ሌሎች ተቋማትም የዩኒቨርስቲውን ፈለግ በመከተል ከማህበረሰቡ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
ስልጠናውን በመስጠት ከተሳተፉት መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ የእጽዋት ሳይንስ ት/ት ክፍል መምህራን የሆኑት መ/ር ሀብታሙ በሪሁን እና መ/ር ታረቀኝ መንግስቱ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰቡ ላቀረበው የድጋፍ ጥያቄ ፈጣኝ ምላሽ በመስጠት ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ቦታው ላይ ላሉ ባለሙያዎችም በቂ የሆነ ስልጠና እንዲሰጥ ማድረጉ ጠቀሜታው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።