መጻሕፍት ለእውቀት ገበታ፣ መዛግብትና የጽሑፍ ቅርሶች ለዘመን ትውስታ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ታላቅ የመጽሐፍ ኤግዚብሽን በዲላ ከተማ ተጀመረ።

ዲ.ዩ የካቲት 12 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ እና ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ታላቅ የንባብ ሳምንት፣ የቡክፌር ፣የኤግዚብሽን እና የፓናል ውይይት ዛሬ በዲላ ከተማ በይፋ ተከፍቷል።
የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዲላ ከተማ ከንቲባ ክቡር አቶ ተስፋጽዮን ዳካ እንኳን ወደ አረንጓዴዋ ሻላይቱ ዲላ በሰላም መጣችሁ በማለት መልዕክታቸውን ካስተላለፉ በኃላ ይህ የንባብ ሳምንት አላማው የትውልዱን የንባብ ባህል በማጎልበት ትውልዱን ብቁ ዜጋ እንዲሆን ማስቻል እንደሆነ ተናግረው ፕሮግራሙ ወጣቱ ትውልድን ከደባል ሱስ ወደ መጻሕፍት ማንበብ እንዲያዘነብል የማድረግ ትልቅ አቅምና ጉልበት ያለው ዝግጅት እንደሆነ ተናግረዋል።
የዕለቱን መልዕክት ያስተላለፉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው አንድ የሰውነት አካል በምግብና በስፖርት እንደሚገነባ ሁላ የሰው ልጅ አዕምሮም የሚገነባው በዕውቀት እና በመጻሕፍት ስለሆነ እነዚህን መጻሕፍት ማንበብ ከቻልን አዕምሮችንን መገንባት ስለምንችል ዕለት ዕለት የማንበብ ልምዳችንን መጨመርና ማሳደግ እንደሚኖርብን ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ አቡቱ አኑቶ በበኩላቸው ንባብ አለምን የመቀየር አቅም ያለው ኃይል እንደሆነ ገልጸው ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመቀየር በሚያስችል ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች ሁሉ መሠረታቸው ንባብ ስለሆነ ይህን የንባብ ባህል እንዲጎለብትና እንዲያድግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ - መጻሕፍት ኤጀንሲ ከክልሉ ቢሮና ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ይህን ዝግጅት በማድረጋቸው በራሴና በክልሉ ቢሮ ስም ላመሰግናቸው እወዳለው ብለዋል።
ዝግጅቱን አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኑ አምላክ መዝገቡ ከ800 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ መጻሕፍትን በዞኑ ለሚገኙ ቤተ መጻሕፍት ለማስረከብ ይዘው እንደመጡ ተናግረዋል::
ከዛሬ የካቲት 12 ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 16 /2014ዓ.ም ለተከታታይ 5 ቀናት በሚቆየው በዚህ የመጽሐፍት ኤግዚብሽን ልዩ ልዩ መጻሕፍት በ50 % ቅናሽ ለሽያጭ ቀርበዋል::
በዝግጅቱ ደራሲ ጋዜጠኛና ሀያሲ ዘነበ ወላ እና አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ ስለንባብ አንቃቂ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም እነሱን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ የሀገራችን የሥነ ጽሁፍ ሰዎችም ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ታውቋል።
በዛሬው የጠዋቱ የመክፈቻ መርሐ ግብር የመጽሐፍት የባዛር ጉብኝት፣ ስለንባብ አነቃቂ ንግግር ፣ የመጽሐፍ ሽያጭ አውደ ርዕይ ፣ የጎዳና ላይ ቡክፌርና የሕጻናት ቤተ - መጻሕፍት ንባብ በይፋ ተከፍቶ የተጎበኘ ሲሆን በከሰዓቱ መርዓ ግብር ደግሞ የጎዳና ላይ ንባብ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የጥያቄና መልስ ውድድር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
*********************
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ገፆችን ይጎብኙ ÷ ትኩስ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ይከታተሉ
..........
ዌብሳይት: www.du.edu.et
ኢሜይል: pirdir@du.edu.et
ቴሌግራም: https://t.me/dprd9
ስልክ: +251 46 131 00 01/+251 46 331 24 61
ፋክስ: +251 46 331 35 16
ፖ.ሳ.ቁ: 419
Dilla University
University of the Green Land!
Dilla, Ethiopia