"መፃሕፍት ለእውቀት ገበታ፤ መዛግብት እና የጽሑፍ ቅርሶች ለዘመን ትውስታ" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ታላቅ የንባብ ሣምንት በዲላ ከተማ እንደቀጠለ ነው::

ዲ.ዩ የካቲት 13/2014ዓ.ም (ሕ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርስቲ ፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መፃሕፍት ኤጀንሲ እና ደቡብ/ብ/ብ/ሕ/ክ/መንግስት ባህልና ቱሪዝም ጋር በመተባበር የተዘጋጀው የንባብ ሣምንት አካል የሆነው በጌዴኦ ዞን ዲላ ማረሚያ ቤት የንባብ ክበብ ምሰረታና ተከናውኗል።
የንባብ ሳምንቱ መርሃ-ግብር ዛሬ ቀጥሎ ሲውል በጌዴኦ ዞን ባህል አደራሽ የሥነ-ጽሑፍ መድረክ በዛሬው ዕለት ተከናውኗል፡፡
"የሰው ልጅ በሆነ አጋጣሚ ወንጀል ሊሰራ ይችላል" ያሉት ኢንስፔክተር ትዕግስት ሮቤ የዲላ ማረሚያ ተቋም ኃላፊ መስሪያ ቤታቸው ከተመሠረተበት 1942 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ታራሚዎችን አንጾና አስተምሮ ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራውን እንደ ቀጠለ ገልፀዋል፡፡
ማረሚያ ተቋሙ ታራሚዎችን በሥነ- ምግባር፣ በትምህርት፣ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ ሥልጠናዎች በማብቃት ለቀጣይ ሕይወታቸው ጥሩ ስንቅ እንደሚያስጨብጣቸው ገልፀዋል፡፡
በዲላ ማረሚያ ተቋም እስከ 8ተኛ ክፍል የደረሰ መደበኛ ትምህርት እንደሚሰጥ አውተሰው ለ8ተኛ ክፍል የሚሰጠው ክልላዊ ፈተናን ታራሚዎች ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘገቡ አደራ ብለዋል። እሳቸው አክለውም በቀጣይ ከትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር 2ተኛ ደረጃ ት/ቤት የመክፈት እቅድ እንዳላቸው በማውሳት የሚመለክተው አካል እገዛ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ መጽሕፍት ኤጀንሲ ተወካይ ወ/ሮ ክብነሽ ገ/ስላሴ በበኩላቸው ለማረሚያ ተቋሙ አንድ ሺህ መጽሕፍት፣ በገንዘብ ሲገመት 150,000 ሽህ ብር (አንድ መቶ ሃምሳ ሽህ ብር) በማስረከብ የንባብ ክበቡ ተመስርቷል፡፡
በዕለቱ በተጋባዥ እንግድነት የተገኙት ደራስያን፣ ገጣሚያን እና አርቲስቶች ስለ ንባብ ጥቅም፣ የቤተ-መጽሕፍት ምንነት እና አስፈላጊነት ላይ ገለፃ አድርገዋል፡፡ እንግዶቹ የንባብ፣ የሕይወት ተሞክሯቸውን ያካፈሉም ሲሆን፣ አነቃቂ ንግግሮችንም ለታዳሚያን አድርገዋል፡፡
የእለቱ መርሃ-ግብር በጌዴኦ ባህል አደራሽ ከተለያዩ ት/ቤቶች የተወጣጡ ተማሪዎች፣ እንግዶች እንዲሁም የሀገራችን እውቅ ደራስያን፣ ገጣሚያን እና አርቲስቶች በተገኙበት ግጥም፣ መነባነብ፣ ትምህርት አዘል ድራማዎች እና በዲላ ዩኒቨርስቲ ባህል ማዕከል ሙዝቃዎችን በማቅረብ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ የንባብ ሳምንቱ እና ተያያዥ ዝግጅቶች ግን በመጪዎቹ ቀናት መካሄዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በትላንትናው ዕለት በጠዋት ምዕራፍ የፕሮግራሙ መክፈቻ ስነስርዓት ተደርጎ በከሰዓት በኃላ ቆይታ በጌዴኦ ባህል አዳራሽ የህፃናት ጥያቄና መልስ ውድድር መደረጉ አይዘነጋም::