በዲላ ከተማ እየተካሄደ ባለው የመጽሐፍት ኤግዚቢሽን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባት ተመስርተዋል::

ዲዩ የካቲት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. (ህ.ግ.) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጽሐፍት ኤጀንሲ እንዲሁም ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክ/መ/ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር “መጽሐፍት ለዕውቀት ገበታ፤ መዛግብትና የጽሁፍ ቅርሶች ለዘመን ትውስታ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ፕሮግራም ዛሬም ቀጥሎ ውሏል። በዛሬው ውሎ የትምህርት ቤቶች የንባብ ክበባትን በመመስረት፣ በማደራጀት እና ልምድ በመለዋወጥ ተግባራት በማተኮር ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
በእለቱ ንግግር ያደረጉት የዲላ ከተማ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ራቦ እንኳን ብዙ ምሁራን ወዳፈራው ዲላ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በሰላም መጣችሁ ሲሉ እንግዶችን ተቀብለዋል።
ኃላፊው አክለውም እየደበዘዘ የመጣውን የንባብ ልምድ ለማነቃቃት “መጽሐፍት ለዕውቀት ገበታ፤ መዛግብትና የጽሁፍ ቅርሶች ለዘመን ትውስታ” የሚል መልዕክት አንግቦ በዚህ ከተማ የተዘጋጀው መርሃ-ግብር "ለእኛ ትልቅ ዕድል ነው" ያሉት አቶ ከፍያለው በእንግድነት የመጡት ደራሲያን እና ታዋቂ የንባብ ሰዎች የንባብ ልምዳቸውን በዲላ ከተማ ተገኝተው በማካፈላቸው ተጠቃሚዎች ነን ብለዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ከዚህ የሚገኙ ትምህርቶች በቀጣይ ብዙ አርቲስቶች፣ ደራሲያን እና የንባብ ሰዎች በከተማችን እንዲፈጠሩ የሚያግዝ ነውም ብለዋል፡፡ አያይዘውም ለዲላ ማረሚያ ተቋም 150 ሺህ ብር የሚገመቱ አንድ ሺህ መጽሐፍትን ጨምሮ በዲላ ከተማ የህዝብ ቤተ-መፃህፍት እንዲሁም ለስምንት ትምህርት ቤቶች ጭምር በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት እና ቤተ-መዛግብት ኢጀንሲ መበርከታቸውን አስመልክቶ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ስነ-ምግባር ሊያንፁ የሚችሉ ጽሁፎችን በማንበብ ራሳችንን በእውቀት በማነፅ፣ ለውጥ የሚፈጥሩ የልማት ስራዎችን በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት መሠረት አበጀ በበኩላቸው የንባብ ክበባት መመስረታቸው ተማሪዎች በትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ ከሚማሩት ትምህርት በተጨማሪ አእምሮአቸውን በንባብ ለመሞረድ ያስችላቸዋል ብለዋል። መምህሩ አክለው እንዳሉት አስተማሪ በሌለበት ቦታና ጊዜ መጽሐፍቶችን ማንበብ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ በተለይ 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የንባብ መሠረት የሚጣልባቸው ቦታዎች እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡
በእለቱም ለተማሪዎች የመጽሐፍት ሽልማት ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡
በዲላ ከተማ ከሚካሄደው የንባብ እና መፃህፍት አውደርዕይ በተጓዳኝ በዛሬው ከሰአት መርሃ-ግብር የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ "ውይይት ከደራሲያን ጋር" በሚል ሀሳብ ተጋባዥ ፀሀፊያኑና የጥበብ ሰዎቹ ከተማሪዎችና መምህራን ጋር ውይይት አካሂደዋል።
የኮሌጁ ዲን ዶክተር እዮብ ቀለመወርቅ በመክፈቻ ንግግራቸው መሰል አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ደራሲያኑን ከተማሪዎችና መምህራን ጋር ማገናኘት ፋይዳው ብዙ ነው ብለዋል። በነበረው ውይይትም ደራሲያን፣ ገጣሚያንና ጋዜጠኞቹ የህይወትና ስራ ተሞክሮአቸውን ለታዳሚያን አጋርተዋል።
ታዳሚያኑ ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይም ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ቀደም ብሎ በነበሩ ክንውኖች የተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተጎበኙ ሲሆን የተለያዩ የንባብ ክበባትም ተቋቁመዋል።
የዚሁ የንባብ ሳምንትና የመፃህፍት አውደ ርዕዩ አካል የሆነው የፓናል ውይይት ነገ ቀጥሎ የሚውል ይሆናል፡፡