ዲ.ዩ. የካቲት 15/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት እና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ፣ ከደቡብ ቤ/ብ/ሕ/ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ዲላ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጁት የንባብና መፃህፍት አውደ-ርዕይ ሳምንት አካል የሆነው በሰነድ፣ መዛግብት እና የፅሁፍ ቅርሶች አያያዝ እና አስተዳደር ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሄደ። በዲላ ከተማ የጌዴኦ ባህል አዳራሽ የተካሄደው

ዲ.ዩ. የካቲት 15/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት እና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ፣ ከደቡብ ቤ/ብ/ሕ/ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ዲላ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ያዘጋጁት የንባብና መፃህፍት አውደ-ርዕይ ሳምንት አካል የሆነው በሰነድ፣ መዛግብት እና የፅሁፍ ቅርሶች አያያዝ እና አስተዳደር ዙሪያ የፓናል ውይይት ተካሄደ።
በዲላ ከተማ የጌዴኦ ባህል አዳራሽ የተካሄደውን የፓናል ውይይት በንግግር የከፈቱት አቶ ዘማች ክፍሌ የጌዴኦ ዞን ትምህርት መመሪያ ኃላፊ እና የዞኑ አስተዳደር ተወካይ ናቸው። ኃላፊው በንግግራቸው እንዳሉት ሰው ለአካላዊ ጥንካሬው መዳበር ምግብ እንደሚሻ ሁሉ ሁሉን አቀፍ እይታና አስተሳሰቡ እንዲዳብር ደግሞ በትምህርት እና ንባብ የዳበረ እሳቤ ያስፈልጋል ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም ከትምህርት ቤት ባለፈ የንባብ ባህልን በማዳበር የህይወት ዘመን እውቀትን ማስፋት ይገባል ብለዋል። የብዙ ዜጎች አእምሮ በንባብና በእውቀት በበለፀገ ቁጥር ሀገር ያለማል ያሉት አቶ ዘማች በተለይ በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን ቁንፅል ሀሳብ ይዞ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልምና እንደ ሀገር ንባብ ላይ ያለንበት ድክመት መሻሻልና ሰፊ የእውቀት አውድ መፈጠር አለበት ሲሉ ይህን ለማገዝ የሚጠቅመው ወይይት መከፈቱን አብስረዋል።
በውይይቱ ላይም በአብያተ-መዛግብት ታሪካዊ አሻራዎችን ከመጠበቅ እስከ ትውልድ ለማስተሳሰር፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መፃህፍት ኤጀንሲ በዲላና አካባቢው የሚገኘው መዛግብት፣ የዲጂታል ቤተ-መፃህፍት የነፃ ሀብት አጠቃቀም፣ የመረጃ ሀብትን ማሰባሰብና ደረጃውን የጠበቀ አዘገጃጀት የማህበረሰብ ተደራሽነት ያለው ጠቀሜታ፣ የመሳሰሉ የውይይት መነሻ ሀሳቦች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት እና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ባለሙያዎች ቀርበዋል።
ከመነሻ ፅሁፍ አቅራቢዎቹ አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ካሱ ንባብ የአስተሳሰብ አድማስን በማስፋት ጠያቂ ማህበረሰብ፣ አሳቢና ተመራማሪ ትውልድ ለመፍጠር የሚረዳ በመሆኑ ሁሉም በጋራ አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር መሰራት ይገባል ብለዋል። በመነሻ ፅሁፋቸው እንዳነሱት ከሆነ የተቋማት እና አብያተ-መፃህፍት በጋራ መስራት በመረጃ ልውውጥ፣ በዋቢ መፃህፍት መጋራት፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና ወቅታዊ መረጃ ልውውጥን በማሳለጥ የተቀላጠፈ የእውቀት መጋራት እድል መፍጠር ይገባልም ብለዋል። ይሁን እንጅ የባለሙያ፣ የሀብት፣ የግንዛቤ እጥረቶች እና የትብብር ማነስ ትብብሩን ለማሳለጥ እንቅፋቶች ናቸው፤ እነዚህን በጋራ መቅረፍ ያስፈልጋልም ብለዋል።
በዲጂታል ቤተ-መፃህፍት አደረጃጀትና አጠቃቀም ዙሪያ መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት አቶ አዲሱ ብርሃኔ በበኩላቸው በመፃህፍት መልክ በወረቀት ከሚኖረው አቀራረብ በተጨማሪ ቤተ-መፃህፍት የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ማዘጋጀት ለአጠቃቀም፣ ለተደራሽነትም አመቺ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በተለይ አሁን የደረስንበት የቴክኖሎጂ ዘመን ንባብን በጊዜ፣ በቦታና በአቀራረብ የበለጠ ቀላል ማድረግን የሚጠይቅ እንደመሆኑ የዲጂታል ቤተ-መፃህፍት በወረቀት ከሚቀርቡ መፃህፍት ባሻገር መፃህፍትን በኮምፒውተር ፅሁፍ፣ ድምፅ ቅጂ እና ምስል ማቅረብ የተቻለበት ሁኔታ ላይ ደርሷል ነው ያሉት።
ሌላኛዋ ጥናት አቅራቢ ወይዘሪት ገነት ተስፋዬ በበኩላቸው የመረጃ ሀብትን ለዛሬውም፣ ለመጪውም ትውልድ ማሰባሰብ የሀገርን ገፅታ ይገነባል፤ ይህን ተገንዝቦ እራሱን በንባብ ያበቃ ትውልድ ደግሞ ሀገርን ይገነባል ብለዋል። ይሄን እውን የማድረጉ ስራ ፍሬ የሚኖረው የመረጃ ሀብትን በአግባቡ ሰብስቦና ሰንዶ ለንባብ ማዘጋጀት በአግባቡ ሲሰራ ነውም ብለዋል።
በውይይቱ በጌዴኦ አካባቢ ዲላ ከተማና ዙሪያዋ ይከናወኑ የነበሩ የመንግስት አስተዳደር፣ የህዝብ አኗኗር እና አጠቃላይ ታሪካዊ ክዋኔዎች ከጥንት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ተሰንደው የሚገኙ የታሪክ ማስረጃዎች ተዳሰዋል።
ውይይቶቹን የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህራኑ ዶክተር ዘላለም ጌታቸው እና አቶ ቴዎድሮስ ቦጋለ መርተዋቸዋል።
ለውይይት መነሻነት በቀረቡት ፅሁፎች እና ባነሷቸው ሀሳቦች ላይም ከታዳሚያን የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል። በተሳታፊዎቹ እንደ ሀገር ለንትርክ መነሻ ምክንያት የሆኑ የታሪክ ሰነዶች አሰናነድና አሰባሰብ እንዲሁም ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት እና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲው በሁሉም ቋንቋዎች፣ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ብሔረሰቦች ታሪክ የሚያሳዩ የመዛግብት አሰባሰብ ስራ እየተሰራ ነው ወይ? ትውልዱን የበለጠ አንባቢ ለማድረግ በንባብና እውቀት የበቁ እናቶች እንዲኖሩ ምን እየተሰራ ነው? የየብሔረሰቡ አፈታረኮች፣ ስነ-ቃሎች፣ ታሪክ፣ ወግ እና ባህላዊ ክዋኔዎች በየ ቋንቋው ተሰንደው ለትውልድ እውቀት ግንባታ እንዲውሉ ትምህርት ቤቶች፣ በየ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍሎች በትኩረት ቢሰሩ፣ እስካሁን በተለያየ መልኩ፣ በተለያየ ቦታ ተከማችተው የሚገኙ የታሪክ ሰነዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ቢያዙ እና ለጥቅም እንዲውሉ ምን ይደረግ? የሚሉ ጥያቄና አስተያየቶች ተነስተዋል።
ለንባብ እና ቤተ-መፃህፍት ያለን የተዛባ አመለካከት ሀገራዊ የንባብ ልምዳችን የዳበረ እንዳይሆን ዳርጎታል ያሉት ተሳታፊዎቹ ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት በሀገር ደረጃ አንድ በማዕከል ከመሆን ወጥቶ ወደ ክልሎች ወርደው ሌሎች ተጨማሪ ቤተ-መፃህፍት ቢከፈቱ የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠትም፣ የበለጠ ለብዙሃኑ ተደራሽም ለመሆን ይጠቅማልና ይታሰብበት ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርስቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው የዲላ ከተማ አስተዳደር የጌዴኦ ዞን ቤተ-መዛግብትን ለመመስረት ጥረት ቢያደርግ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የሚጠበቅበትን እገዛ ሁሉ ያደርጋልም ሲሉ የዩኒቨርስቲውን ዝግጁነት አሳውቀዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎችም መነሻ ሀሳብ አቅራቢዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ የብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት እና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ባለሙያ አቶ ተስፋዬ ካሱ በምላሻቸው ለንትርክ መነሻ ይሆናሉ የተባሉ ሰነዶችን አስመልክቶ ኤጀንሲው ስራው በየትኛውም ሁኔታ የተሰነዱ ማስረጃዎችን መሰብሰብ ነው፤ ነገር ግን በክፍትና በዝግ ለንባብ የሚቀርቡበትን አሰራር በመዘርጋት “አጨቃጫቂ” ናቸው የሚባሉ ሰነዶችም ታሪካዊ ፋይዳ አላቸው፤ ኤጀንሲው ሰንዶ ያስቀምጣል። በታሪኮ ላይ ጥናት ለሚሰሩ ግን እንዲመረምሯቸው እድል ይፈጥራል ብለዋል።
አቶ ተስፋዬ አክለውም በየቦታዎቹ ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍት እና መዛግብት እንዲኖሩ ይገባል፤ ግን የአቅም ውስንነቱ ጉዳይ እና እንደ ሀገር ያለን ትጋት ማነስ ታክሎበት ያ አልሆነም። ወደ ፊት ግን ብዙ ስራዎች ይጠብቁናል ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ መምህሩ ቴዎድሮስ ቦጋለ በበኩላቸው በቤተ-መፃህፍት ሰራተኞች ስነ-ምግባር፣ ትጋትና እውቀት ላይ በተለያዩ ጊዜና ቦታዎች የሚያውቋቸውን ትጉሃን ባለሙያዎች የስራና የህይወት ልምድ እያጣቀሱ ሀሳብ አካፍለዋል። መምህር ቴዎድሮስ አክለውም ቤተ-መፃህፍት ሰራተኞች መፃህፍትን ነፍስ እንዳለው ሰው ያህል ሊጠነቁቁላቸው፣ መፃህፍቱን ጠንቅቀው ሊያውቁ እና ሊጠብቋቸው ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ መጨረሻም ዋጋቸው 800,000 ብር የሚያወጡ ስድስት ሽህ የተለያዩ መፃህፍት በዲላ ከተማ እና አካባቢው ለሚገኙ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስጦታ መልክ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መፃህፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ ተበርክቷል። መፃህቱን የኤጀንሲው የመረጃ ሀብቶች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሪት ክብነሽ ገብረስላሴ ለጌዴኦ ዞን ትምህርት መመሪያ ኃላፊ አቶ ዘማች ክፍሌ አስረክበው ውይይቱ ተጠናቋል።
**********************
**********************
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ገፆችን ይጎብኙ ÷ ትኩስ እና ወቅታዊ መረጃዎችን ይከታተሉ
..........
ዌብሳይት: www.du.edu.et
ኢሜይል: pirdir@du.edu.et
ቴሌግራም: https://t.me/dprd9
ስልክ: +251 46 131 00 01/+251 46 331 24 61
ፋክስ: +251 46 331 35 16
ፖ.ሳ.ቁ: 419
Dilla University
University of the Green Land!
Dilla, Ethiopia