የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት አባላት ተማሪዎችን ለመቀበል ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ያለውን የሀሴ ዴላ ካምፓስ ጉብኝት አካሄዱ።

ዲ.ዩ የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት አባላት አራተኛ ካምፓስ በሆነው ሀሴ ዴላ ካምፓስ ተገኝተው የመስክ ጉብኝት አካሄዱ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በተመራው በዚህ ጉብኝት ወቅት ካምፓሱ ተማሪ ለመቀበል ያለውን ቅድመ ዝግጅት ምን እንደሚመስል በየዘርፉ ያሉ ኃላፊዎች ማብራሪያ ለማኔጅመንቱ የሰጡ ሲሆን የሀሴ ዴላ ካምፓስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ፍርዴ በበኩላቸው በአሁኑ ሰዓት ግብዓቶችን ለማቅረብ ጨረታ ያሸነፉ ድርጅቶች አንዳንድ ግብዓት ማዘግየት ካልሆነ በስተቀር የፊንሽንግ ስራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ተናግረው እነዚህ ድርጅቶችንም ቢሆን በአካል እስከ ተቋሟቸው ድረስ በመሄድ በፍጥነት ግብዓቶችን እንዲያቀርቡ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ታምራት አክለውም በዚህ አመት 1200 ወንዶችንና 800 ሴት በድምሩ 2000 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚሆን ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ኘሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ኢንጅነር በፍቃዱ መኩሪያ በበኩላቸው የውሃ መስመር እና የአጥር ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜ በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ እንደሆነ ተናግረው ነገር ግን የመብራት ዝርጋታው እና የውስጥ ለውስጥ መንገድ ስራው በተወሰነ ደረጃ መጓተት ስለሚታይባቸው እነሱ ላይ በትኩረት እና በፍጥነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ከማኔጅመት አባላቱም በካምፓሱ አጠቃላይ ዝግጅት ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ከኃላፍዎች አስፈላጊው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶ መግባባት ላይ ተደርሳል።
በስተመጨረሻም የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ዛሬ እዚህ የተገኝነው ካምፓሱ ተማሪ ለማስገባት ያለውን ቅድመ ዝግጅት ለመመልከት እንደሆነ ተናግረው በዚህም የተሰሩ ስራዎች ጥሩ እንደሆኑና አንዳንድ ያልተሟሉ ግብዓቶች እንዲሁም ከሰው ሀይል ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ማለቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የካምፓሱን የስራ ሂደት ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራርና የማኔጅመንት አባላት ተመልክተዋል።