ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀውን የማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ዘርፍ የቀድመ-ምረቃ ሥርዓት ትምህርት በመቅረፅ እና በማስተባበር ለተሳትፉ ባለ ድርሻ አካላት የምስጋና ዕውቅና ፕሮግራም አከናወነ::

ዲ.ዩ የካቲት 17/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) በ2013 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ዘርፍ የቅድመ-ምረቃ ስርዓት ትምህርት በመቅረፅ እና በማስተባበር ለተሳተፉ ባለ ድርሻ አካላት በዛሬው እለት የምስጋና እና እውቅና ምስክር ወረቀት መስጠቱን ዲላ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ። የእውቅና መርሃ-ግብሩን የዩኒቨርስቲው ማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ አስተባብሮ አዘጋጅቶታል፡፡
ማሕበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ በዩኒቨርሲቲያው ካሉ ኮሌጆች አንጋፋ እና በውስጡ የያዛቸው ትምህርት ክፍሎችም ሰፊ ናቸው ያሉት ዶ/ር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አገራችንና ተቋማችን የሰጣችሁን ሀላፊነት በብቃት ስለተወጣችሁ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ትምህርት ሚኒስተር እና በዩኒቨርሲቲው ስም አመሰግናለው ብለዋል፡፡
ዶክተር ችሮታው አክለውም ከቀጣይ ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ተማሪዎች በሀገር ደረጃ የብቃት ማረጋገጫ መውጫ ፈተና (Exit exam) ስለሚወስዱ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ፍቃዱ ወ/ማሪያም በዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ስራው አድካሚ እንደ መሆኑ ብዙ ውጣ ውረድ ታልፎ ለዚህ ቀን በመድረሳችን ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡ እሳቸው አክለውም ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር በተቀናጀት መልኩ ስለ ሰራ ለዚህ ውጤት በቅተናል ነው ያሉት፡፡
ዶ/ር እዮብ ቀለመወርቅ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማሕበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ኮሌጅ ዲን በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የማሕበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብዕ ዘርፍ ስርዓተ ትምህርት ቀረፃ እና ዝግጅት ላይ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ሀገራዊ ኃላፊነቱን ወስዶ በማስተባበር ስራውን በብቃት ተወጥቷል ብለዋል፡፡
በዚህ ሂደት 47 መምህራን እና አምስት አስተባባሪዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመናበብ በሁሉም ሀገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚጠቀሙባቸው 55 የትምህርት ፕሮግራሞችና በትምህርት ፕሮግራሞቹ የሚሰጡ የኮርስ ዝርዝሮች አጥንቶ አፀድቋል ሲሉ የኮሌጅ ዲኑ አክለው ገልፀዋል፡፡
ከተሸላሚዎች መካከል መምህር አወቀ ፀጋዬ በጥናቱ የተሳተፉ መምህራንና አመራሮች ብዙ ቢደክሙም ዩኒቨርሲቲው እንደዚህ ዓይነት እውቅና መስጠቱ እንዳስደሰታቸው ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡
በእለቱም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው የማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ-ሰብዕ ዘርፍ ሥርዓተ ትምህርት ቀርጻ ለተሳተፉ ባለ ድርሻ አካላት የዕውቅና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡፡