የዲላ ዩኒቨርሲቲ እፅዋት ጥበቃ እና ኢኮቱርዝም ማዕከል "የኢኮቱርዝም ልማት ለአከባቢ ብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እና ለስራ ዕድል ፈጠራ" በሚል መሪ ቃል ውይይት አካሄደ::

ዲ.ዩ. የካቲት 19/2014 ዓ ም (ህ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ እፅዋት ጥበቃ እና ኢኮቱርዝም ማዕከል "የኢኮቱርዝም ልማት ለአከባቢ ብዝሃ-ሕይወት ጥበቃ እና ለስራ ዕድል ፈጠራ" በሚል መሪ ቃል ውይይት አካሄደ። በውይይቱም የዲላ ከተማ፣ አባያ እና ዳራ ወረዳ አመራር አካላት ተሳትፈዋል።
የአካባቢ ብዝሃ-ሕይወት ለመጠበቅ የተፈጥሮን ጸጋ በምርምር በመለየት ወደ ሀብትነት መቀየር ይገባል። ስለሆነም አመራሮች እና የአከባቢው ማህበረሰብ ስለ ብዝሃ-ሕይወት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማዲረግ፣ የኢኮቱርዝም አገልግሎትን ለማጠናከር ታስቦ ነው ይህ ውይይት የተዘጋጀው ብለዋል አቶ ምትኩ ማኑዳ የዲላ ዩኒቨርሲቲ እፅዋት ጥበቃ እና ኢኮቱርዝም ማዕከል ዳሬክተር።
በውይይቱም ማዕከሉ ምን እየሰራ እንዳለ እና እየገጠሙት ያሉትን ሰው ሰራሽ ችግሮች በጋራ ለመፍታት በቀጣይ በውይይቱ ከተሳተፉ አመራሮች ጋር ለመስራት ለታሰበው ስራ መደላድል መፍጠር አንዱ አላማ መሆኑን ዳይሬክተሩ አክለው ገልፀዋል።
የጌዴኦ ዞን ደን እና አከባቢ ጥበቃ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ታደሰ በበኩላቸው የዲላ ዩኒቨርሲቲ እየሰራ ያለው ስራ "እጅግ የሚያስደስት ነው" በማለት በቀጣይ አብረው ለመስራት ቃል ገብተዋል።
በውይይቱ ከተሳተፉት አመራሮች መካከል የአባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከበደ አሬር እየታየ ያለው ለውጥ "አኩሪ በመሆኑ" ማዕከሉም ሆነ ዩኒቨርሲቲው ለሚጠይቁት እገዛ፣ እንዲሁም አብሮነት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
አቶ ከበደ አክለውም በአከባቢው ለሚያስፈልገው ጥበቃ እና ድጋፍ በቁርጠኝነት እገዛ ለማድረግ ተግተን እንሰራለን ብለዋል።
የዳራ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የአስተዳደሩ ተወካይ አቶ ወሰን ዳንጋም ደግሞ "ዛሬ በሩቅ አከባቢዎች ሲሰራ እያየን የሚደንቀን የአከባቢ ጥበቃ እኛው ጋር፣ አጠገባችን ማየት መቻላችን ትልቅ ለውጥ ነው" ብለዋል። ይሄ ስራ የበለጠ ውጤት ያመጣ ዘንድም የዲላ ዩኒቨርሲቲ እፅዋት ጥበቃ እና ኢኮቱሪዝም ማዕከሉን በሶስት አቅጣጫ የሚያዋስኑት አካባቢዎች አመራር አካላት በጋራ ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ መስራት ይቻላል ብለዋል።
ከሀዋሳ ብዝሃ-ሕይወት የመጡት አቶ አለምነው ሙጬ እስካሁን ባላቸው ምልከታ የዚህ አይነት የእፅዋት ጥበቃ ማዕከል ያለው ከፍተኛ ትምህርት ተቋም አለማየታቸውን ገልፀው፣ በቀጣይ ማዕከሉን በሀገር አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ፣ ከሌሎች ቦታዎችም ልምድ በመውሰድ አሁን ካለበት የተሻለ ከፍ በማድረግ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል ብለዋል።
የእፅዋት ጥበቃ እና ኢኮቱሪዝም ማዕከሉን በጋራ በመጠበቅ እና በማስፋት ላይ በሚሰሩ የጋራ ጉዳዮች ላይ አዋሳኝ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በባለጉዳይነት እንዲሰሩ ሀሳብ በመለዋወጥ ውይይቱ ተጠናቋል።