የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ በግንባታ ላይ ያሉትን የአስተዳደር ህንፃ እና ሀሴዴላ ግቢ ጎበኘ::

ዲ.ዩ የካቲት 19/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ እና የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር የ2014 ዓ.ም የስድስት ወር እቅድ ክንውን ላይ ውይይት ካካሄደ በኋላ በኦዳያአ ግቢ የሚገኘውን የአስተዳደር ህንፃ እና የሀሴዴላ ግቢ አጠቃላይ የግንባታ ሂደት ጎብኝቷል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ አንጋፋ ከሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በመሆኑ ተቋሙን የሚመጥን የአስተዳደር ህንፃ መገንባቱ የሚያስደስት ነው ያሉት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አብዮት ደምሴ፣ ግዙፉ የአስተዳደር ህንፃ ከዚህ በፊት የነበረውን የቢሮ እጥረት በመቅረፍ እና ምቹ የስራ ቦታ በመፍጠር እረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ቦርዱም ዩንቨርሲቲው የሚሰራቸው ስራዎች ላይ የቅርብ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስ እና ልማት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮናስ ሰንዳባ በበኩላቸው ተቋሙ ከጀመራቸው በርካታ ግንባታዎች መካከል ዛሬ በስራ አመራር ቦርዱ እና የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራር የተጎበኙት የአስተዳደር ህንፃ እና ሀሴዴላ ጊቢ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በጉብኝቱም የአስተዳደር ህንፃው መጠናቀቁን እና በቅርብ ጊዜ ርክክብ እንደሚካሄድ የገለፁ ሲሆን የሀሴዴላ ጊቢም በዚህ ዓመት ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ጽ/ቤት ኃላፊ ኢንጂነር በፍቃዱ መኩሪያ በበኩላቸው በኦዳያአ ግቢ የሚገኘው የአስተዳደር ህንፃ በ2010 ዓ.ም ግንባታው መጀመሩን ገልፀው በዚህ ሰዓት ግንባታው እንደተጠናቀቀ እና በቅርቡ ወደ ስራ እንደሚገባ አስረድተዋል። ህንፃው ባለ ስድስት ወለል ሆኖ የቢሮ፣ የካፍቴሪያ አገልግሎት፣ የስብሰባ አዳራሾች እንዲሁም የፓርኪንግ አገልግሎት ሁሉ ለመስጠት እንዲያስችል ተደርጎ ተገንብቷል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የግንባታ ኢንቨስትመንት እየተደረገበት ያለው የሀሴዴላ ጊቢ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ስድስት ፎቆች እና ሌሎች መካከለኛ እና አነስተኛ ህንፃዎች በመገንባት ላይ እንዳሉ አቶ በፍቃዱ አክለው ገልፀዋል።
ይሄው አዲስ ግቢ አራት ሺህ ተማሪዎች ለመቀበል አቅም እንዲኖረው ታቅዶ እየተሰራ ያለ ቢሆንም በዚህ ዓመት ከአጠቃላይ የመቀበል አቅሙ ግማሹን ማለትም ሁለት ሺህ ተማሪዎች ለመቀበል ዝግጁ ነው ተብሏል።