የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞቾ ልማት ድርጅት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ጋር በመተባበር ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ።

ዲ.ዩ የካቲት 21/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞቾ ልማት ድርጅት ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ጋር በመተባበር ለተማሪዎች ስልጠና ሰጠ። ስልጠናው በአካል ጉዳተኝነት አና አካታችነት ጽንሰሀሳብ ዙሪያ ከየኮሌጁ ለተውጣጡ ጉዳት አልባ ተማሪዎች ተሠጥቷል፡፡
ተማሪዎች በጋራ በሚኖሩባቸው ቦታቸው፣ በመማሪያ ክፍላቸውና በእለት ተዕለት የጊቢ እንቅስቃሴያቸውም ሆነ ወደ ስራ አለም ሲቀላቀሉ በአገልግሎት አሰጣጥ ለሚያገኟቸው አካል ጉዳተኞች የሚኖራቸው መስተጋብር የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ ታልሞ መዘጋጀቱን የልዩ ፍላጎት ት/ት ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር አባቡ ተሾመ ገልጸዋል።
ዶ/ር አባቡ አክለውም ስልጠናው የተዘጋጀው በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች የልማት ድርጅት (ECDD) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ከየኮሌጆች የተውጣጡ ሰላሳ ሰልጣኞች ተሳታፊ ናቸው ብለዋል፡፡ ስልጠናው ለሁለት ቀናት የተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል::
ሰልጣኞች ከስልጠናው በኃላ አካል ጉዳተኞችን ለማገዝ ሲሞክሩ የቋንቋ አጠቃቀማቸውም ሆነ የአካል ንክኪያቸው ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆንም ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሚኖራቸው የአብሮነት ጊዜ አካል ጉዳተኛውን የማያስቆጣና ለተደራቢ ጉዳት የማይዳርግ እንዲሆን ግንዛቤያቸውን የተሻለ ለማረግ እንደሚያግዝ ገልፀዋል።
በስልጠናው ተሳታፊ የነበረችው የሶስተኛ አመት የአዋላጅ ነርስ ተማሪ ሃይማኖት ምትኩ ከስልጠናው አካል ጉዳተኛን ‹‹እንዴት›› ማካተት እንዳለብን ግንዛቤ የጨበጥን ሲሆን ከዚህ በፊት በነበረኝ ልምድ ከአካል ጉዳተኛ መምህራኖቼ ብርታትን ጥንካሬን እና ጽናትን ተምሬባቸዋለሁ ብላለች፡፡
ወደፊት አሁን ባገኘችው ስልጠና ከአካል ጉዳተኛ ወገኖቿ ጋር እንዴት መደጋገፍ እንደሚቻል በቂ ግንዛቤ በማግኘቷ በስራም ሆነ በትምህርት አካታችነትን በአግባቡ እተገብራለሁ ብላለች።
ሌላኛው የሁለተኛ ዓመት የስርዓተ ትምህርት ተማሪ ያሬድ አለማየሁ ስልጠናው በፊት ስለ አካል ጉዳተኛ የነበረውን አመለካከት እንደቀየረውና አካል ጉዳተኛን ለማገዝ ምን አይነት ቃላትን መጠቀም እንዳለት ግንዛቤን ሰጥቶኛል ያለ ሲሆን ተማሪዎችም አካል ጉዳተኛን ከአይችሉም ስሜት ወጥተው በመቀራረብ ቢተጋገዙ ይጠቀማሉ ብሏል፡፡
በመጨረሻም ዶ/ር አባቡ ለልጠናው ተማሪዎችን በመመልመሉ ሂደት ፈጣን ምላሽ ለሰጡ ኮሌጆች ምስጋናን ያቀረቡ ሲሆን የስልጠናው ተሳታፊ የነበሩ ተማሪዎችን እንዲሁም የስልጠናው አስተባባሪ የነበሩ የቢሮ ሰራተኞችን አመስግነዋል።