126ኛ አመት የአድዋ ድል መታሰቢያ በአል ምክንያት በማድረግ ዶክተር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ያስተላለፉት መልዕክት

"ለመላው ኢትዮጵያዊያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች፦ እንኳን ለ126ኛ አመት የአድዋ ድል መታሰቢያ በአል በሰላም አደረሳችሁ።
ይህንን በአል ስናከብር ጥንት አባቶቻችን የውጪ ጠላት በመጣ ጊዜ የውስጥ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው የውጪ ወራሪን በአንድነት ተፋልመው ድል እንዳደረጉ ሁሉ፣ ዛሬም ሐገራችን ወጥረው የያዟት ዘርፈ ብዙ የውጪ እና የውስጥ ጠላቶች አሏት። ዛሬም ሐገራችን አንድነቷን የሚፈታተን ፍልሚያ አለባት። ዛሬም ሐገራችን በአንድነት ቁመን እንድንታገልላት፣ ክብሯን፣ ነፃነቷን እንድናስጠብቅላት፣ በልዩነታችን እየተገፋፋን ለጠላት እድል ከማስፋት ይልቅ በአንድነታችን እየተደጋገፍን በህብረት ቁመን ዘርፈ ብዙ ድል እንድናጎናፅፋት ትሻለች።
በወቅቱ ጠላት ደንበር አቋርጦ መጥቶ የሐገርን ነፃነት እና ክብር ለማኮሰስ ጦርነት በከፈተብን ጊዜ አያቶቻችን መለኞች፣ አስተዋዮች ስለ ነበሩ የሁላቸውም በሆነው ጠላት ላይ ለመዝመት አንድነትን አፀኑ።
ንጉሰ ነገስቱ አፄ ምኒልክ በክተት አዋጃቸው "አመልህን በጉያህ፣ ስንቅህን በአህያህ ይዘህ ተከተለኝ" ያሉት በውስጥ ከነበሩ ጥቃቅን ልዩነቶች በላይ የጋራ ህልውናን የሚያጠፋ ጠላት መጥቷልና አመላችንን በጉያችን ደብቀን በአንድነት እንዝመት ሲሉ ነበር።
ለድላችን የሚያበቃንን ስንቃችንን በአህያችን ሲሉም፣ የጥንካሬያችን መሰረት የሆነውን አንድነታችንን፣ ህብረታችንን እንጅ ልዩነታችንን አናጉላው ማለታቸው ነበር። አመል በልዩነት ሲመሰል፣ ስንቅ በአንድነት፣ በጥንካሬ ተመስሎ ነበር ለውድ ኢትዮጵያዊያን የታወጀላቸው። እነሱም ሰሙ፣ በህብረትም ተመሙ፣ አድዋም የመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ፍለጋ ትግል ተምሳሌት ሆነ።
ዛሬ ሐገራችንን አደጋ ላይ የሚጥል ማንኛውም ሁኔታ ሲገጥመን በአንድነት በመቆም የሐገራችንን አንድነት ጠብቀን አያቶቻችን ለአባቶቻችን፣ አባቶቻች ደግሞ ለእኛ እንዳወረሱን ሁሉ እኛም ለቀጣይ ትውልድ እንድናስተላልፍ ጥሬዬን አቀርባለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!"
ዶክተር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት