በዲላ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ምግባር ምንነት ፅንሰ ሃሳብና አስፈላጊነት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና አዲስ ለተቀጠሩ መምህራን ተሰጠ::

ዲ.ዩ. የካቲት 24/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ምግባር ምንነት ፅንሰ ሀሳብ እና አስፈላጊነት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና አዲስ ለተቀጠሩ መምህራን ሰጠ።  የዩኒቨርሲቲው የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ከሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ጋር በመሆን ነው ስልጠናውን ያዘጋጁት።
መምህራን ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ስለ ተቋሙ አጠቃላይ ገፅታና ባህሪ እንዲሁም የመንግስት ሠራተኞች የሚመሩበትና የሚተዳደሩበትን ህግና ደንቦች ማሳወቅ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ስልጠናው የተሰጠው ተብሏል።
አዲስ ገቢ መምህራኑ በቀጣይ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲሰሩ እና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን ስልጠና አግኝተዋል ብለዋል፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሀብት አስተዳደርና ልማት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ፀጋ፡፡
ስልጠናውን ሲሰጡ ያገኘናቸው የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ዜጋ እና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ተስፋዬ መኮንን በበኩላቸው የተሰጠው ስልጠና አዲስ ለተቀጠሩ መምህራን የስነ-ምግባር ምንነትንና ጠቀሜታ አውቀው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በመምህርነት በሚሰሩበት ጊዜ ተገቢውን ስነ-ምግባር ተከትለው ለማህበረሰቡ መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡
መምህር ተስፋዬ አክለውም አጠቃላይ የሆነ ስነ-ምግባር መርህን፣ የሙያ ስነ-ምግባር እና ውሳኔ ለመስጠት ሊጠቀሟቸው የሚገቡ ዋና ዋና ፅንሰ ሃሳቦች ላይ ያተኮረ ስልጠና ነው የተሰጠው ብለዋል። እንደ መምህርነታቸው በዩኒቨርሲቲው በሚቆዩባቸው ጊዜ ሁሉ ሊከተሏቸው ስለሚገቡ ስነ-ምግባሮች እንዲሁም ማድረግ ስለሌለባቸው ነገሮች በዝርዝር እንዲያውቁ መደረጉ ተገልጿል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ቡድን መሪ አቶ ታምሩ ተሾመ በበኩካቸው በሀብት ማሳወቅ እና ምዝገባ አስፈላጊነት ቅድመ አሞላል ላይ በስልጠናው ለተሳተፉ እና አዲስ ለተቀጠሩ መምህራን ገለፃ ሰጥተዋል፡፡