በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሴት መምህራንን የምርምር ስራዎች ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ያለመ ምክክር ተካሄደ::

ዲ.ዩ. የካቲት 25/2014 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሴት መምህራንን የምርምር ስራዎች ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ ያለመ ምክክር ተካሄደ። የምክክር መድረኩ በዩኒቨርሲቲው የስርአተ-ፆታ ዳይሬክቶሬት ከምርምር እና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ጋር በትብብር የተዘጋጀ ነው።
ያለ ሴቶች ተሳትፎ የሚያድግ ሀገርም ሆነ ህብረተሰብ የለም ያሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሴ/ህ/ወ/ጉ ዳይሬክተር ወ/ሮ አለሚቱ ብርሃኑ ጽ/ቤታቸው ዩኒቨርሲቲው በሚያዘጋጀው ስትራቴጂክ እና ዓመታዊ እቅዶች ላይ የሴት መምህራን እና ተመራማሪዎች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ግቦች የበለጠ ትኩረት እንዲያገኙ እንሰራለን ብለዋል።
ኃላፊዋ አክለውም አመልካች ግቦችን በማስቀመጥ ሊለኩ የሚችሉና በውጤታማነት የሚተገበሩ እቅዶች እንዲዘጋጁና እንዲተገበሩ የሚያስችሉ ስራዎች ላይ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ሴት መምህራን ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ የሚጠበቅባቸው የምርምር ስራዎች ላይ ተሳትፎአቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲያበረክቱ እየተሰራ ነው ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ እስካሁን የተሰራው ስራ በቂ አለመሆኑ ስለታመነበት ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ለሴት መምህራን መድረክ በማዘጋጀት ክፍተቶች ተለይተው በማስተካከል ለቀጣይ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚረዳ ውይይት በማስፈለጉ ነው ይህ የምክክር መድረክ የተዘጋጀው ብለዋል ወ/ሮ አለሚቱ።
በዲላ ዪኒቨርሲቲ የምርምርና ስርፀት ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብታሙ ተመስገን በበኩላቸው ሴቶች ከወንዶች ይልቅ የተፈጥሮ እና የማህበረሰብ ጫና እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። ዶ/ር ሀብታሙ አክለውም ከተፅዕኖዎቹ ባሻገር ሴት መምህራን በምርምር ስራዎች ላይ እየተሳተፉና ውጤታማ ስራዎች እየሰሩ ቢገኙም ተሳትፎአቸውን ከዚህ በላይ ከፍ ለማድረግ ዳይሬክቶሬቱ በስልጠና፣ በምክክር እና በገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
የሚደረገው ድጋፉም ሴቶች ብቁ እና ተወዳዳሪ ተመራማሪዎች እንዲሆኑ ፋይዳ እንዳለው የምርምርና ስርፀት ዳይሬክተሩ ዶ/ር ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድኩ ከተሳተፉ መምህራን መካከል ወ/ሮ ናርዶስ ኤሊያስ እና ወ/ሮ እታፈራው በቀለ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሴት መምህራን በምርምር የበኩላቸውን ተሳትፎ እንዲያደርጉ እንደዚህ አይነት መድረክ ማዘጋጀቱ ሊመሰገን ይገባል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ሴት መምህራን እርስ በራሳቸው የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና የሙያ ስልጠና እንዲያገኙ መድረኮች ቢዘጋጁ የተሻለ የልምድ እና እውቀት ሽግግግር መፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
ተሳታፊ መምህራኑ አክለውም በመድረኩ የተገኙ እውቀቶችና ልምዶች ወደ ፊት የተሻለ የምርምር ስራ ለማከናወን ያግዛሉ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።