የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ የተፈጥሮ ሀብት እና ግብርና ስራዎችን በተቀናጀ ሁኔታ እያከናወነ መሆኑን ገለፀ::

የዲላ ዩኒቨርሲቲ በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ መሰረት የተግባር ተኮር (Applied) ዩኒቨርሲቲ ምደባ ውስጥ የተካተተ ነው። በዚህም መሰረት ዩኒቨርስቲው በትኩረት ከሚሰራባቸው መስኮች መካከል የግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ዋነኛው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ዩኒቨርሲቲው ለአካባባው ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂና የክህሎት እገዛ ለማድረግ ከአካባባው ማህበረሰብ ፍላጐት ጋር የሚጣጣም ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት አካባባ ጥምር ደን ግብርና እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደር ሥልተ ምርት የሚከናወንበት በመሆኑ የልማት እገዛ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ስራዎችን ያከናውናል፡፡ ከዚህ አኳያ በጥምር የደን ግብርና ሥራ ዙሪያ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ የአካባቢ ዝርያዎች የመጠበቅና የዝርያ ማሻሻል ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ከዚህም በተጨማሪ የተሻሻሉ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮቹ በማለማመድ ከግብርና ስራቸው ሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የተሻለ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸው ለማስቻል እየሰራ ነው፡፡ በመሆኑም ላለፉት አስራ አራት አመታት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር መንደርን እንዲሁም በይርጋ ጨፌ ወረዳ ዶማርሶ አካባቢ የሚገኘውን የማህበረሰብ አገልግሎት ተደራሽ ፕሮጀክት በማቋቋም የደጋ ፍራፍሬ፣ ቡና፣ ቅመማቅመም፣ እንሰት እና የቡና ጥላ ዛፎች የማልማትና የማባዛት ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ተቋሙ የአካባቢው ማህበረሰብ ያሉበትን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ለይቶ በጥናትና ምርምር ለመፍታት በትኩረት እየሠራ ነው፡፡
የአካባቢውን ማህበረሰብ ማገልገል የተቋሙ ዋነኛ ዓላማ ሲሆን አገልግሎቱን ለማስፋት እና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ዩኒቨርሲቲው የዕውቀት ሽግግር፣ ክህሎትን ማሳደግና በጥናትና ምርምር የተመሠረተ አገልግሎት በመስጠት የማህበረሰቡን ምርታማነት ከፍ ማድረግ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መንገድ እንደሆነ በመረዳት ከዚሁ ጋር የተገናኙ አስቻይ ሁኔታዎችን ዘርግቶ የተግባር ውጤት እያስመዘገበም ነው፡፡ ይህን ውጤትም የበለጠ ለማሳደግ ካለፉት ተግባራት ልምድ መቅሰም፣ የተሻሉ ግኝቶችን ማስፋት እና ክፍተቶችን ማረም ላይ የቀጣይ ትኩረት ማዕከል ነው።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በደቡብ ክልል የማህበረሰብ ተደራሽ ፕሮጀክቶችን በማቋቋምና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በመስጠት የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይም ነው። ለአብነትም ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ፣ በሽታን ተቋቁመው የተሻለ ምርት ማስገኘት የሚችሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በሳይንሳዊ ዘዴ በማዘጋጀት፣ ያረጁና አርሶ አደሩ በልማዳዊ አሰራር የሚጠቀምበትን ቡና በአዲስ ወጣት ቡና ለመተካት በማለም ዩኒቨርስቲው በምርምር ላይ የተመሰረተ ተግባር እያከናወነ ነው። ለዚህም በምርምር በመታገዝ ከ160 ሺህ በላይ የቡና ችግኞችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የተሻሻለው ዝርያ ከመሠራጨቱ በፊት ዘመናዊ አሠራርን ተግባራዊ በማድረግ የቡና እና ቅመማ ቅመም ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል በንድፈ ሃሳብና በተግር የተደገፈ ስልጠና ለአርሶ አደሮች ይሰጣል፡፡ አርሶ አደሮቹም በስልጠና ያገኙትን እውቀት በልምድ ካካበቱት የግብርና ጥበብ ጋር በማጣጣም የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚያስችል የተግባር ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ። ዲላ ዩኒቨርሲቲ ዘርፉን በማዘመን አዳዲስ አሰራሮችን በማላመድና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በምርምር በመፍታት የቡና ምርታማነትን ለማሻሻለ በመስራት አካባቢያዊ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ፋይዳ ያለው የግብርና ማዘመን ተልዕኮውን በላቀ ብቃት እየተወጣ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ደረጄ አንዱዓለም የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን ገለፃ የግብርናው ልማት ሥራ ከአርሶ አደሩ በተጨማሪም የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ከግምት ውስጥ ያስገባ የእንስሳት ልማትን የሚያግዝ ሳይንሳዊ ስራ ሌላኛው ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው። በመሆኑም ነጻ የእንስሳት ክትባት አገልግሎት መስጠት፣ የተቀናጀ ዓሣ ሀብት ልማት፣ አትክልትና ዶሮ እርባታዎች የሚያገለግሉ ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ማስተማር፣ የንብ እርባታን በማሻሻል እንዲሁም የተሻሻለ የወተት ከብት እርባታን በማስተዋወቅ ከጥምር የደን ግብርና ጋር ተስማምቶ እንዲተገበር በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ስለሆነም አርሶ እና አርብቶ አደሩ ከአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ጋር የተስማማ የግብርና ልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ዘርፎቹን በምርምር መምራት አይነተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ዩኒቨርስቲው ይህን ያለመ የተግባር ስራ መከወኑ ለማህበረሰቡ የተሻለ ምርታማነትን አስገኝቷል። በኑሮው ላይም መሻሻሎች እየታዩ፣ ለቀጣይ ስራ ግብአት መሆን ጀምረዋል።
ከግብርና ትምህርት ተደራሽነት አንጻር የአካባቢ ማህበረሰብን በጥናት ምልከታ በማሳተፍ፣ የተሻሉ ችግር ፈቺ የሚሆኑ የትምህርት ፕሮግራሞችን በመክፈት ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ባሉ የግብርና የሙያ ዘርፎች የትምህርት ዕድል እንዲያገኝ የተጀመሩ ስራዎች ቀጣይነት ባለው መልኩ መተግበራቸውን ቀጥለዋል ይላሉ ዶክተር ደረጄ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ አጫጭር የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን ለባለሙያዎች፣ ለአርሶ እና አርብቶ አደሮች፣ ለሚመለከታቸው አስተዳደር አካላት ወዘተ በመስጠት የክህሎት እና የዕውቀት ሽግግር እየተፈጠረም ነው፡፡
ይህን ወደፊት የበለጠ በማስፋት፣ በማዘመን እና በተሻለ ተደራሽነት በመተግበር የህብረተሰብን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ስራ መስራቱን ዩኒቨርሲቲ አጠናክሮ ይቀጥላል።
***********************
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
የካቲት 08 ቀን 2014 ዓ.ም