የዲላ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ እና ምህንድስና ኮሌጅ ስር የኪነ-ህንፃ ምህንድስና ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ ተማሪዎችን አስመረቀ::

ዲ.ዩ መጋቢት 3/2014 ዓ.ም. (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂ እና ምህንድስና ኮሌጅ የኪነ ህንፃና የግንባታ ምህንድስና ትምህርት ቤት የኪነ-ህንፃ ምህንድስና (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡
የቴክኖሎጂ እና ምህንድስና ኮሌጅ መምህራንና ኃላፊዎች እንዲሁም የተማሪ ወላጆች እንግዶችና ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በታደሙበት ነው ምረቃቱ የተካሄደው።
ለዚህ ለ5ተኛ ዙር የኪነ-ህንፃ ምህንድስና ተማሪዎች የምረቃ መርሃ ግብር እንኳን አደረሳችሁ ያሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በ1989 ዓ.ም. በሁለት ኮሌጆች 400 ተማሪዎችን ተቀብሎ መማር ማስተማር ስራ እንደ ጀመረ ገልፀዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው አክለውም በአሁኑ ወቅት በአይነትም በጥራትም ሰፊ የማስፋፋት ስራ በመስራት በሶስት ካምፓሶች ላይ 59 በዲግሪ ፕሮግራም፣ 46 በማስተርስ ፕሮግራም እና 4 በዶክትሬት ፕሮግራም በጥቅሉ ከ28,000 በላይ ተማሪዎችን ዩኒቨርሲቲው ተቀብሎ የሚያስተምርበት አቅም ላይ መድረሱን ገልፀው አራተኛ ጊቢውን ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዳዊት አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ምረቃዎችን አከናውኖ ከ80,000 በላይ ብቁ ባለሙያዎችን ለሀገር ማበርከቱን ገልፀው በዛሬው እለት የተመረቁትን የኪነ-ህንፃ (አርክቴቸር) ምህንድስና ተማሪዎች እንደ ወላጅም እንደ አስተማሪም ሆነው እስከዚህ ድረስ ላበቁ መምህራኖች ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አያይዘውም ተማሪዎች በቆይታቸው ወቅት ቤተሰባዊነት ተሰምቷቸው፣ የተለያየ ችግር ቢኖርም ግቢ ውስጥ በሰላም ተምረው በሰላም እንዲጨርሱ ላበቁት ለዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ሠራተኞች፣ ለዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ እና ለአካባቢው ህብረተሰብም በተመሳሳይ መልኩ ምስጋና አቅርበዋል።
ዶ/ር ዳዊት አክለውም ተመራቂ ተማሪዎች በተለያዩ ችግሮች አልፋችሁ፣ በሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ውስጥ የራሳችሁን አስተዋጽኦ አድርጋችሁ፣ ችግሮችንም አሸንፋችሁ ለዚህ ቀን ስለበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እያንዳንዱ ምሩቅ ካለው አገራዊ ሁኔታ አንፃር መንግስታዊ ስራ ብቻ የማይገኝበት በመሆኑ የራስን ስራ ከመፍጠርም አንፃር ሰፊ ርብርብ እንዲያደርግ አሳስበው ለተመራቂ ተማሪዎች ቀጣይ ዘመናቸው ብሩህ እንዲሆን ዶ/ር ዳዊት ተመኝተው ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
በምረቃ መርሃግብሩ ያነጋገርናቸው እና በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ተሸላሚ የሆኑት ተማሪ ኪሩቤል ገቢሳ እና ተማሪ ሳምራዊት ገብሬ ይህን የላቀ ውጤት የማምጣታቸው ምክንያት በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው በበለጠ ትጋት እና የዓላማ ቁርጠኝነት እለት ተእለት ተግተው ትምህርታቸው ላይ በመስራታቸው እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡
በዛሬው እለትም በመደበኛ መርሃ-ግብር የኪነ-ህንፃ ምህንድስና እና ሌሎች ተመራቂዎችን ጨምሮ 76 ወንድ፣ 30 ሴት፣ በድምሩ 106 ተመራቂዎች፣ በክረምት ተከታታይ መርሃ-ግብር 167 ወንድ፣ 29 ሴት፣ በድምሩ 196 ተመራቂዎች፣ እንዲሁም በድህረ-ምረቃ መርሃ-ግብር 85 ወንድ፣ 11 ሴት፣ በደምሩ 96 ተመራቂዎችን ጨምሮ በጠቅላላው ወንድ 328፣ ሴት 70፣ በአጠቃላይ ትምህርታቸውን ተከታትለው ያጠናቀቁ 398 ተመራቂዎች ተመርቀዋል።