ዲላ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን እየተቀበለ ነው

ዲ.ዩ፦ መስከረም 27/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን ከትላንት 26/2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተቀበለ ነው።
ዩኒቨርሲቲው በሁለት ዙር በጥቅሉ 20 ሽህ አካባቢ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስፈትን ሲሆን፣ አሁን ላይ በመጀመሪያ ዙር የሚፈተኑ ከ16 ሽህ በላይ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎችን ነው እየተቀበለ ያለው። በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የሚመራ አብይ እና በምክትል ፕሬዝዳንቶች የሚመሩ ንዑሳን ግብረ-ኃይሎችን አቋቁሞ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱንም መዘገባችን ይታወሳል። በመፈተኛ ክፍል ዝግጅት፣ በተማሪዎች ምኝታ ቤት፣ በምግብ እና የህክምና አገልግሎት መስጫ የስራ ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች የፈተናውን ሂደት ውጤታማ ለማድረግ በሚያግዙ ተግባራት ሲከናወን የነበረው ዝግጅት በስኬት ተጠናቋል። ከትላንት ጀምሮም ከደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን እና አጎራባች አካባቢዎች እንዲሁም ከሲዳማ ክልል ተፈታኝ ተማሪዎችን፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየመጡ ያሉ ፈታኝ መምህራንን እና የፈተና አስፈፃሚ ባለሙያዎችን እየተቀበለ ይገኛል። የፈተናውን አጠቃላይ ሂደት ደህንነቱን የተጠበቀ ለማድረግ የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ሲሆን ከፌዴራል ፖሊስ እና የክልል ፖሊስ ኃይል ጋርም የቅንጅት ጥበቃ እየተከናወነ ነው።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
25 ዓመታትን ትውልድ በመቅረፅ ጉዞ!