የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የመጀመሪያ ዙር በሰላም መጠናቀቁ ተገለፀ

ዲ.ዩ፦ ጥቅምት 02/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሶስቱም ግቢዎች ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሰላም ተጠናቋል።
በዋናው፣ ኦዳያአ እና ሐሴዴላ ግቢዎች ከተፈተኑት ከ16 ሽህ 800 በላይ ተማሪዎች መካከል ከቅርብ ርቀት የመጡት ተማሪዎች ወደየ አካባቢያቸው እየተሸኙ ሲሆን ሌሎች በተያዘላቸው የጉዞ መርሃግብር መሰረት የሚሸኙ ይሆናል።
የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ ከተወሰነ ጀምሮ በተቋሙ መዋቅር፣ የፀጥታ አካላት፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የአካባቢው አስተዳደር እና የሚመለከተው ባለ ድርሻ አካላት ሁለ ተሳትፎ ያደረጉበት ዝግጅት እንደ ነበር የገለፁት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንትና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ዶ/ር ፍቃዱ ወ/ማርያም ናቸው።
በቂ ዝግጅት በመደረጉም የመጀመሪያው ዙር ፈተና በሰላም መጠናቀቁን ነው ዶ/ር ፍቃዱ የገለፁት። በተጠናቀቀው ፈተናም ለሁለተኛው ዙር የሚሆን በቂ ልምድ በማገኘታችን ቀጣዩ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፈተናን በብቃት እንወጣዋለን ብለዋል።
ዶ/ር ፍቃዱ አካለውም ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላረጉ ፈታኝ መምህራን፣ የፈተና አስተባባሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ የግቢው ማሕበረሰብ እና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ምስጋና ይገባቸዋልም ነው ያሉት።
የፈተናውን ሂደት ለመቆጣጠር ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡት አቶ አበበ ጥላሁን በበኩላቸው ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ ከተፈታኝ ተማሪዎች ስነ-ምግባር ጀምሮ፤ ፈታኝ መምህራን፣ የፈተና አስተባባሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር እና ሰራተኞች በቅንነት እና በታታሪነት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ብለዋል።
ፈተናውም ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን ገልፀው የፈተና ስርቆት እና ማጭበርበር በከፍተኛ ደረጃ የሚከስምበት መንገድ ተጀምሯል ነው ያሉት። በመሆኑም ትውልድ እና ሀገርን ከፍ ለማድረግ ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልፀዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛው ዙር (ተፈጥሮ ሳይንስ) ከደቡብ ብ/ብ/ሕ/ ክልል ጌዴኦ ዞን እንዲሁም ከአጎራባች የሲዳማ ክልል የሚመጡ ሶስት ሽህ አካበቢ ተማሪዎችን ተቀብሎ የሚያስፈትን ይሆናል።