የ‹ሲ.ቲ ስካን› ማሽን ስራ መጀመሩ ተገለጸ

ዲ.ዩ፡- ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገዛው የ‹ሲ.ቲ ስካን› ማሽን ስራ መጀመሩ ተገለጸ፡፡ ሆስፒታሉ የህክምና ስራዎቹን ለማሳለጥ እና ተደራሽነት ለማስፋት ከሚጠቀመው ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች አንዱ መሆኑን ነዉ የተገለጸው። በዩኒቨርሲቲው የሕክምና እና ሳይንስ ኮሌጅ እና ጠቅላላ ሆስፒታል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ምጽዋ ሩፎ ሆስፒታሉ ከጌዴኦ ዞን፣ ኦሮሚያ እና ሲዳማ አጎራባች ክልሎች ለሚመጡ ከፍተኛ ቁጥር ላለው ሕብረተሰብ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ጠቅሰዋል፡፡ ለሕብረተሰቡ ከሚሰጣቸው የህክምና አገልግቶች በተጨማሪ ሆስፒታሉ በጤና ዘርፍ ተማሪዎችን በተለያዩ የሕክምና ሙያ መስኮች ተቀብሎ እያስተማረ እና እያሰለጠነ እንደሚገኝም ዶ/ር ምፅዋ ገልፀዋል፡፡ እሳቸው አክለውም አዲስ የተገዛው ‹ሲ.ቲ ስካን› በዚህ ሳምንት ስራ ጀምሯል ብለዋል፡፡ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እና ጠቅላላ ሆስፒታል የተግባር እና ስልጠና ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቢኒያም ወያ በበኩላቸው ‹‹በሆስፒታሉ ስንጠቀምባቸው ከነበሩ ማሽኖች ራጅ፣አልትራሳውንድ እና ሌሎች በደረጃ ከፍ ያለውን ሲ.ቲ ስካን ስራ መጀመሩ ተቋሙን አንድ ርምጃ ወደ ፊት የሚያሻግር›› መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዶ/ር ቢኒያም አከለውም የህክምና መሳሪያው ወደ አገልግሎት መግባት ታካሚዎች ወደ ሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል እና ሌሎች የግል ሆስፒታሎች ይላኩ የነበበትን ሁኔታ የሚለውጥ ነው፡፡ ይህን አገልግሎት ለማገኘት ወደ ሐዋሳ ይላኩ የነበሩ ህሙማንን ከእንግልት፣ ወጪና ጊዜ ብክነትም የሚያድን እንደሆነ ነው የተገለጸው::
የራዲዮሎጂ ትምህርት ክፍል ሀላፊ የሆኑት ዶ/ር ኤርሚያስ ተረፈ ህክምና መሳሪያው በቂ የሰው ሃይል ተሟልቶለት በአመቺ ቦታ ስራ መጀመሩን ጠቅሰው የሲ.ቲ ስካን ምርመራ ለሚፈልጉ ደንበኞች ‹‹24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት በራችን ክፍት ነው›› ብለዋል።
በጠቅላላ ሆስፒታሉ የነርቭ እና ጀርባ ስፔሻሊስት ሃኪም የሆኑት ዶ/ር አንተነህ ታደሰ በበኩላቸው የህክምና መሳሪያው ወደ ስራ መግባት ታካሚዎች በቅርቡ አገልግቱን እንዲያገኙ፣ በተለይም በአደጋ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ታካሚዎች ችግሩን ለይቶ የቀዶ ጥገና ሕክምና ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ብለው፡፡
ከዚህ በፊት ‹‹ከ80 በመቶ በላይ ሪፈር የምንጽፍላቸው ለሲ.ቲ ስካን ምርመራ ነበር›› ያሉት ዶ/ር አንተነህ፣ አሁን ግን ታካሚዎች ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን በሚቆጥብ መልኩ በሆስፒታሉ ህክምናውን ማገኘት እንደቻሉ አብራርተዋል።
.................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
25 ዓመታትን ትውልድ በመቅረፅ ጉዞ!