የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርደ በዩኒቨርሲቲው ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ከተቋሙ ከፍተኛ አመራር ጋር ተወያየ

ዜና ትንታኔ ዲ.ዩ፡- ህዳር 03/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ በዩኒቨርሲቲው የ2014 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም እና የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ዝርዝር ውይይት አካሄደ፡፡ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢዋ እና የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ እና የስራ አመራር ቦርዱ አባላት በውይይቱ ተገኝተዋል፡፡ በእለቱ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በአራቱ የምክትል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤቶች፣ በህክማና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል እንዲሁም የፕሬዝዳንት ፅ/ቤት እና በስሩ ያሉ ባለ ብዙ ዘርፍ ፅ/ቤቶች ባለፈው አመት ያከናወኗቸው ተግባራት አፈፃፀም ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡ በዝርዝር ሪፖርቶቹ በአመቱ የታቀዱ፣ የተከናወኑ ተግባራት እንዲሁም በአፈፃፀም የተገኙ እምርታዎች እና ጉድለቶች ከተወሰዱ መፍትሄዎች ጋር በዝርዝር ተዳስሰዋል፡፡ የበጀት ዓመቱን የመማር ማስተማር ተግባራት ዝርዝር ሪፖርት ያቀረቡት የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍቃዱ ወ/ማርያም በዓመቱ ተቋሙ በሀገር ደረጃ ‹‹አፕላይድ ሳይንስ›› ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንደ መመደቡ ይህንኑ ልየታ መሰረት አድርጎ ወደ ትኩረት አቅጣጫ ያደሉ ተግባራት ለመሰራት መሞከሩን አስረድተዋል፡፡ በሪፖርቱ መማር ማስተማር፣ መምህራን ልማት እና አሉማናይ አገልግሎቶች ላይ ያተኮሩ ተግባራት ተብራርተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሁሉም የትምህርት መርሃግብሮች በ2014 የበጀት አመት ከ25 ሽህ 900 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተማረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 93.4 በመቶ ገደማ ያህሉ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ይህም በሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ያለው ዝቅተኛ የተማሪ ቅበላ መሻሻል የሚገባው መሆኑ ቀሪ ስራ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ ወደ ፊትም እንደ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲነቱ በሁሉም የትምህርት መስኮች የሚቀበላቸው ተማሪዎችን ከትኩረት አቅጣጫዎቹ አንፃር ወስኖ ለመስራት ማቀዱን ዶ/ር ፍቃዱ አብራርተዋል፡፡ በልታው መሰረት በአፈፃፀም የተመዘገበው 93.4 በመቶ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 85 በመቶ ቀንሶ በአንፃሩ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ቁጥርን ለማሳደግ መስራት ይጠበቃል ብለዋል የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡ በበጀት ዓመቱ ከልየታ ትኩረት አቅጣጫው ጋር በሚጣጣም መልኩ የስርአተ ትምህርት ክለሳ፣ ፍተሻ እና ቀረፃ የተከናወነ ሲሆን፤ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በ65 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 45 የሁለተኛ ዲግሪ እና አራት የሶስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ተማሪ ተቀብሎ እያስተማረ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በመምህራን ልማት እረገድ በዓመቱ 176 መምህራን ለተጨማሪ ትምህርት የተላኩ ሲሆኑ ከእነዚ መካከል 30 የሚሆኑት የሶስተኛ ዲግሪ የሚማሩ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ በአንፃሩ የደረጃ እደገትን በሚመለከት በአመቱ ያለው አፈፃፀም አሃዝ ከአጠቃላይ የተቋሙ መምህራን አንፃር ሲሰላ 11.7 በመቶ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 78.4 በመቶ ሁለተኛ ዲግሪ እና 9.9 በመቶ ደግሞ ሶስተኛ ዲግሪ ያላቸው እንዲሆኑ መደረጉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በደረጃ እደገቱ በትምህርት አፈፃፀም ከተሰጠው በተጨማሪ በበጀት አመቱ በምርምር ስራዎቻቸው 18 መምህራን ወደ ረዳት እና ተባባሪ ፕሮፌሰርነት አድገዋል ነው የተባለው፡፡ በሂደትም የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው መምህራንን ከዚህ በታች ለመቀነስ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ ዶ/ር ፍቃዱ በምላሻቸው ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም እንደ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የመምህራን ደረጃ የመጀመሪያ ዲግሪ አምስት በመቶ፣ ሁለተኛ ዲግሪ 85 በመቶ እና ሶስተኛ ዲግሪ 15 በመቶ እንዲሆን የሚጠበቅ በመሆኑ ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ ስራ እየተሰራ መሆኑን ነው ዶ/ር ፍቃዱ የገለፁት፡፡ የቦርድ አባላቱም አሃዙ ጥሩ ሂደት ላይ እንዳለ የሚያሳይ ቢሆንም በቶሎ ግቡን ለመምታት ግን ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ተግባራትን በመፈጸም ሂደት ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የጊዜ ሰሌዳ አለመጣጣም የመማር ማስተማር ስራውን በተረጋጋ ሁኔታ ለማስኬድ ችግር እንደነበር ተለይቷል፡፡ ይሁን እንጅ በከፍተኛ ጥንቃቄና ትኩረት የጊዜ ሰሌዳ ተሰርቶ ወደ ተግባር በመገባቱ ይህን የጊዜ ሰሌዳ መዛባት በተሻለ ሁኔታ ማስተካከል መቻሉ ተገልጿል፡፡ ቀጥሎ በምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት እረገድ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት በሚያደርግባቸው ጤና፣ መምህራን ትምህርት፣ ግብርና እና ተፈጥሮ ሃብት ላይ አተኩሮ ምርምር ማካሄድና ቴክሎጂ የማሸጋገር ስራ መሰራቱን ደግሞ የዘርፉ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ በሪፖርታቸው አብራርተዋል፡፡ እንደ እረሳቸው ማብራሪያ በምርምር ስራዎች እረገድ በበጀት አመቱ 129 የምርምር ፕሮጀክቶች ጸድቀው ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ብለው ተጀምረው የነበሩ 49 ምርምሮች በ2014 መጠናቀቃቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በአንፃሩ በበጀት አመቱ ከቀረበው የአፈፃፀም ሪፖርት እንደተመላተው በአነስተኛ እና መካከለኛ ምርምር ፕሮጀክቶች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ የታተሙ የምርምር ውጤቶች ላይ ከእቅድ በላይ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ በበጀት አመቱ በሌሎች የመርምር አውዶች የአፈፃፃም መሻሻሎች ቢታዩም ከፍተኛ የምርምር ፕሮጀክት አፈፃፀም ላይ ውስንነት መኖሩ ታይቷል ነው ያሉት ዶ/ር ደረጀ በሪፖርታቸው፡፡ የተሰሩ ምርምሮችን ከማስረጽ አንፃር በአመቱ የሳይንስ ሳምንት ኩነት፣ ህትመቶች፣ ሀገር አቀፍ የምርምር ጉባኤዎች ተከናወነዋል፡፡ የምርምር ስራዎችን በተሻለ ሁኔታ ለመከወን የሚረዱ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን በተለይ ደግሞ የሴት ተማራማሪዎችን አቅም ከፍ ለማድረግ የሚረዱ ልዩ ልዩ ስልጠናዎች በአመቱ መሰጠታቸውን ዶ/ር ደረጀ አክለው አንስተዋል፡፡ በፕሮጀክቶች ማህበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ የዘርፉ መሰረታዊሰ ስራ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ በአፕል፣ ቡና፣ እነሰት፣ ቅመማቅመም፣ የደጋ ቀርቀሃ፣ ድንች እና በመሳሰሉ ልማቶች ላይ ያተኮሩ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት፡፡ በእነዚህ ሰብሎች ላይ ትኩረት አድርጎ በተሰሩ ስራዎች ከ453 ሽህ 400 በላይ ችግኞት ለማህበረሰቡ በነፃ ተሰራጭተዋል፡፡ የቦርድ አባላቱ በዘርፉ ከከቀበው ሪፖርት በመነሳት ዩኒቨርሲቲው ችግኝ አልምቶ ከማሰራጨት ባለፈ በምርምር እና ጥናት የተሻሻሉ ሰብሎችን በማልማት የአርሶ አደሩን ህይወት የሚለውጡ እና ችግር ፈቺ የሆኑ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ እውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ እንዲያተኮር ጠይቀዋል፡፡ ዶ/ር ደረጀ በሰጡት ማብራሪያ ችግኝ የማሰራጨቱ ስራ ከማህበረሰቡ በሚቀርብ ፍላጎት የሚተገበር እንጅ የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ ስራም በዘርፉ ችግር ፈቺ ምርምሮችን በመስራት የማህረሰቡን የሳይንሳዊ እውቀት እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውስንነት መፍታት ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ላይም ፅ/ቤታቸው ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፐሬዝዳንቱ ዶ/ር ዳዊት ሀዬሶ በበኩላቸው በበጀት አመቱ የዩኒቨርሲቲውን 1.5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት በማፀደቅ ስራዎችን በምዕራፍ ለይቶ ለመፈፀም ወደ ስራ ተገብቶ እንደ ነበር ገልፀዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ አጠቃላይ የመማር ማስተማር ስራውን ለማከናወን የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ከመስራት ጀምሮ በአመቱ መጨረሻ ተማሪን አስመርቆ እስከ መሸኘት ድረስ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በበጀት አመቱ ከህዳር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በቴክሎጂ የተደገፈና የዘመነ አሰራር በተለይ በክፍያ ስርአት ላይ መተግበሩ በጥሩ አፈፃፀም ተጠቅሷል። በዚሁ አሰራር ዩኒቨርሲቲው ሁሉንም የክፍያ ስርአቶች ወደ ኢንተርኔት የክፍያ ስርአት በመቀየር የአጠቃላይ አመታዊ በጀቱን 70 በመቶ ክፍያዎች በኢንተርኔት ስርአት ማከናወን መቻሉን ዶ/ር ዳዊት ገልፀዋል፡፡ በዘርፉ በርካታ ተግባራት ታቅደው የተከናወኑ ሲሆን የተሸከርካሪ እጥረት፣ እንደ ሀገር ካጋጠመው የኢኮኖሚ ጫና ጋር በተያያዘ ጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ በግዥ ሂደቱ የሚስተዋሉ የዋጋ ተለዋዋጭነት የመሳሰሉት ጉዳዮች በበጀት አመቱ ለተመዘገቡ የአፈፃፀም ጉድለቶች ምክንያት ነበሩ ብለዋል፡፡ በቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት በበጀት አመቱ ከግንባታ ስራዎች፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም መዘመን እና ከሃብት ማመንጨት ስራዎች ጋር በተያያዘ የተከናወኑ ተግባራት በዝርዝር በምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ዮናስ ሰንዳባ አማካኝነት ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ዶ/ር ዮናስ ለዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት አመቱ በፅ/ቤታቸው ስር የሚገኙ ስድስት ዳይሬክቶሬት ተግባራትን አብራርተዋል፡፡ ዶ/ር ዮናስ በሪፖርታቸው በተለይም በሐሴዴላ የመማርያ እና የተማሪ ምኝታ ህንፃዎች፣ በህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ በኦዳያአ ግቢዎች እንዲሁም በመምህራን መኖሪያ ቀደም ብለው ተጀምረው በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች በአመቱ ያስመዘገቡትን አፈፃፀም አብራርተዋል፡፡ በኦዳያአ ግቢ ያለውን የአስተዳደር ህንፃ ጨምሮ በሐሴዴላ ግቢ የሚገኙ በርካታ ህንፃዎችን በተሸለ አፈፃፀም ደረጃ በማድረስ በብዛት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን አብራርተዋል። በአንፃሩ የሚቀሩ የማጠናቀቂያ ስራዎችን በትኩረት ተከታትሎ የማስፈፀም ስራ በበጀት አመቱ እተሰራ እንደተመጣም በአሃዝ የተደገፈ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ ይሁን እንጅ በተለይም በሆስፒታል ግቢ ከአዲሱ የህክምና እና ማስተማሪያ ህንፃ እና በኦዳያአ ከሚገነባው የመምህራን መኖሪያ ግንባታ መጓተት ጋር በተያያዘ አሁንም ደካማ አፈፃፀም መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡ በስራ አመራር ቦርድ አባላቱም ደካማ አፈፃፀም የታየባቸው ፕሮጀክቶች ላይ ማብራሪያ ተጠይቆ ዶ/ር ዮናስ ለክፍተቶቹ መኖር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ዮናስ ማብራሪያ በየጊዜው እየናረ ከመጣው የግብአት ዋጋ ልዩነት ጋር በተያያዘ ከፕሮጀክት መነሻ በጀት አንፃር በሂደት እያጋጠመ የመጣ አለመጣጣም፣ ስሚንቶን ጨምሮ የግንባታ ግበአቶች እጥረት በሀገር ደረጃ ማጋጠሙ፣ በግንባታ ቦታዎች የሚነሱ የቦታ ይገባኛል ጉዳዮች ቶሎ እልባት አለማገኘት፣ ከውጭ ለሚገቡ ግብአቶች የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲሁም የተቋራጮች በገቡት ውል መሰረት ስራዎችን መፈፀም አለመቻል የመሳሰሉ ጉዳዮች ለፕሮጀክቶች መዘግገት አይነተኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል በበኩሉ ከትምህርትና ምርምር ባለፈ በዋናነት በህክምና አገልግሎት በርካታ ማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራትን ማከናወኑ ተጠቅሷል፡፡ ሪፖርቱን ያቀረቡት የኮሌጁ እና ጠቅላላ ሆስፒታል ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ምፅዋ ሩፎ በሆስፒታሉ ለደንገተኛ፣ ተመላላሽ፣ ፅኑ ህሙማን፣ ጨቅላ ህፃናት እና የእናቶች ጤናና ወሊድ አገልግሎት ዘርፎች ላይ በርካታ አገልግቶች መሰጠታቸውን አስረድተዋል፡፡ በተለይም በኤች.አይ.ቪ ኤድስ እና ኮቪድ-19 ምርመራ እና ህክምና ስራዎች ላይም ተኩረት ተሰጥቶ የተሰራ ሲሆን ከህክምናው ጎን ለጎን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም ተከናውነዋል ብለዋል፡፡ ይሁንና በሆስፒታሉ የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታ ልኬት ዙሪያ እና የአገልግሎት ማሻሻል፣ ሆስፒታሉን ከህክምና አገልግሎት ባሻገር እንደ ማስተማሪያ ሆስፒታልነቱ ከምርምር ስራዎች ጋርም አስተሳስሮ መስራት እንደሚገባ የቦርድ አባላቱ አሳስበዋል፡፡ ዶ/ር ምፅዋ በበከላቸው ከዚህ ቀደም በሆስፒታሉ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ የአገልግሎት ጥራት ጉድለቶችን ለማስተካከል በሀገር ደረጃ በተመረጡ ሆስፒታሎች መተግበር የተጀመረውን የአገልግሎት አፈፃፀም ትራንስፎርሜሽን መመሪያ መተግባር መጀመሩን ገልፀዋል። የጤና ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ባስቀመጠው ምከረ ሃሳብ መሰረትም በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች እየተወሰዱ ነው ብለዋል፡፡ ለአብነትም በዋናነት የአዲሱ ሆስፒታል ግንባታ እስኪጠናቀቅ ላለመጠበቅ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራርና በሆስፒታሉ ስራ አመራር ቦርድ በኩል ትኩረት ተሠጥቶት ነባሩን ሆስፒታል የማሻሻልና የማደስ ፕሮጀክት ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉን ገልፀዋል፡፡ ስራው በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን ገልፀው በተጨማሪ ቀድመው ይነሱ የነበሩ ከመድሃኒት እጥረት ጋር የተያያዙ ችግሮች ተፈትተዋል ብለዋል። ቀድሞ ወደ ሌሎች ይላኩ የነበሩ ህሙማንን በሆስፒታሉ አስቀርቶ ለማከምም ተጨማሪ የህክምና መሳሪያዎች ግዢ ተፈፅሞ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል ዶ/ር ምፅዋ። ለአብነትም የአጥንት፣ ጀርባና ነርፍ ቀዶ ህክምና አገልግሎቶችን አዲስ ወደ ስራ ባስገቡት "ሲቲ ስካን" መስጠት ተጀምሯል ተብሏል። በሌላ በኩል በዘርፎች ደረጃ ተከፋፍሎ በዝርዝር በቀረበው የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት የፕሬዝዳንት ፅ/ቤት በስሩ ያሉትን የበርካታ ዳይሬክቶሬት ፅ/ቤቶችን ዝርዝር አፈፃፀም ሰብሰብ አድርጎ አቅርቧል፡፡ በፅ/ቤቱ ስር በተለይም በህግ አገልግሎት ከማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት ጎን ለጎን በተለያዩ ህግና ህግነክ ጉዳዮች ስራዎች መሰራታቸው ተመላክቷል፡፡ በተለይም በልዩ ልዩ የፍርድ ሂደቶች የዩኒቨርሲቲውን ጥቅም ያስጠበቁ፣ የሃብት ብክነትን ያስቀሩ፣ ተቋሙን ያላግባብ ሃብት እንዲያጣ ሊያደርጉ የነበሩ የፍርድ ቤት ጉዳዮችን እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ድረስ በመሄድ በበርካታ ሚሊዮን ብር የሚጠጉ ያልተገቡ ቅጣቶችን ማሸነፍ መቻሉ በስኬት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በፅ/ቤቱ ስር ከሙስና መዋጋት፣ ህዝብ ግንኙነት፣ ተቋማዊ መረጃን ለሚዲያ ተደራሽ በማድረግ ገፅታ የመገንባትና መረጃ ማድረስ፣ ቅሬታ መቀበልና ተገቢ መፍትሄ መስጠት፣ የተለያዩ ዘርፎችን የውስጥ ኦዲት ማከናወን፣ ግዥና ንብረት አስተዳደር፣ የተቋሙን የውስጥ ገቢ ከማሳደግ፣ ከባህል ማዕከል፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ህፃናት ላይ ያተኮሩ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መሳይ ፍቅሩ ለስራ አመራር ቦርድ አባላቱ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ የስራ አመራር ቦርድ አባላቱም በቀረቡላቸው ዝርዝር የአፈፃፀም ሪፖርቶች ላይ አስተያየቶች የሰጡና ጥያቄዎች ያቀረቡ ሲሆን ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አማራር አካላትም በየዘርፉ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የስራ አመራር ቦርዱ ፀሐፊ ዶ/ር ችሮታው አየለ በሰጡት ማጠቃለያ ምላሽ በ2014 በጀት አመት ከወትሮው በተለየ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ መከናወኑ፣ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት በገንዘብ፣ በአይነትና በህክምና ሙያ ድጋፍ መደረጉ፣ በጦርነት ተጎድተው የነበሩትን የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በማድረግ በግብአት የማሟላት ስራ መሰራቱ እና የቆቦ ሆስፒታልን መልሶ ስራ ለማስጀመር ድጋፍ መደረጉን እንደ ጥሩ ተግባራት አንስተዋል፡፡ ዶ/ር ችሮታው አክለውም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ለምርምርና ልማት የሚውል 46.9 ሄክታር መሬት ርክክብ ተደርጎ ወደ ስራ መገባቱን፣ የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ትምህርት ቤት ግንባታ በማከናወን ጥራቱን እና የቅበላ አቅሙን የማሻሻል ስራ መሰራቱ እና ወደ ስራ ማስገባቱ ስኬቶች ናቸው ብለዋል። ዶ/ር ችሮታው አክለውም ከሰራተኛ እና ስራ ምደባ ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ የሰራተኛ ቅሬታዎችን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ መቻሉን፣ በእፅዋት ጥበቃና ኢኮ-ቱሪዝም እንዲሁም በቡና ምርምር ማዕከል ማቋቋም ስራዎች ላይ ለሀገር ኢኮኖሚ ጭምር ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት ለማከናወን መሰረት መጣሉ ‹‹ትልቅ ስራ ያከናወን ስለመሆናችን ማሳያ ናቸው›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጅ እንደ ሀገር ወደ ፊት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እራሳቸውን እንዲችሉ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ‹‹እኛም ከወዲሁ የእራሳችንን ገቢ በማመንጨት እራሳችንን ለመቻል በሰፊው እንሰራልን›› ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለውም እንደ ተቋማ በበጀት አመቱ በታዩ የአፈፃፀም ክፍተቶች ላይ አተኩረን ችግሮቹን ከወዲሁ በመቅረፍ በ2015 በጀት አመት የተሻለ ውጤት ለማመጣት በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል፡፡ ለዚህም የተከበረው ቦርድ አስፈላጊ እገዛ እንዲያደርግልን ከወዲሁ እንጠይቃለን ሲሉ ዶ/ር ችሮታው በአፅንኦት ጠይቀዋል፡፡ የስራ አመራር ቦርድ አባላቱ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በሚከፍታቸው የትምህርት መርሃግብሮች፣ በሚቀበላቸው ተማሪዎች፣ በሚያከናውናቸው ምርምሮች እና አቅዶ በጀት በሚይዝባቸው ስራዎች ሁሉ በልየታ የተሰጠውን የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲነት ተልዕኮዎች እና የትኩረት አቅጣጫዎች ለማሳካት በሚያስችለው ሁኔታ መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ በበርካታ ዘርፎች ዩኒቨርሲቲው አበረታች ስራዎች አከናውኗል ብለዋል። በይበልጥ ግን ስራዎች በተጨባጭ ምን ችግር ፈቱ፣ ምን ውጤት አመጡ የሚለው ጉዳይ ዋነኛ መለኪያ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡ ክብርት ሰብሳቢዋ አክለውም በተለይም የክፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቅርቡ በአጭር ጊዜ ዝግጅት በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ብሔራዊ ፈተና አስፈትነው በስኬት ማጠናቀቃቸው ምን ያህል የመፈፀም እምቅ አቅም እንዳላቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ይህንን እምቅ አቅም በሌሎች መደበኛ ስራዎቻቸው ላይ በማዋልም የተሻለ ሀገርና ህዝብ የሚጠቅም ስራ እንዲሰሩ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲም በሪፖርቱ የታዩ የመፈፀም አቅሞቹን በይበልጥ ትኩረት ሰጥቶ የጎደሉት ነገሮች ላይ ደግሞ በግለፅ ችግር ፈቺ የሆነ ስራ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል ሰብሳቢዋ፡፡ በተለይም ከእቅድ አኳያ ጥርት ያለ፣ ተጨባጭ እና ሊለካ የሚችል ውጤት የሚያመጣ ስራ መሰራት ያለበት ሲሆን፣ ሴቶችን በምርምር ስራዎች ተሳታፊ ማድረግ፣ አቅማቸውን ማጎልበት፣ የምርምር በጀትን በአግባቡ ችግር ፈቺ በሆኑ እና በታለመለት ቦታ ማዋል ላይ፣ የማህበረሰብን ችግር በመፍታት ለውጥ መፍጠር የሚችሉ ምርምሮችን መስራት በትኩረት መያዝ ያለባቸው ስራዎች ናቸው ብለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፃ በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች በብዙ ነገሮች ከህዝቡም ከመንግስትም ቀድመውና ከፍ ብለው መገኘት አለባቸው፤ ስለሆነም ከግለሰብ ይልቅ ሀገርን እና ህዝብን ለሚጠቅሙ ሀሳቦችና ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት ወሳኝ በመሆኑ ዲላ ዩኒቨርሲቲም በዚህ አግባብ መጓዝ አለበት በለዋል፡፡ የቦርዱ አባል እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ስርአት ችግር የማካፈል ስራ የሚሰራበት እንጅ ችግር ፈቺ አልነበረም፤ በተለይ ሁሉንም ዩኒቨርሲቲች በየቦታው የማዳረስ እንጅ በተለዩና በውስን ዘርፎች ላይ ልቀው እንዲወጡና ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጥባቸው አድርጎ የመቅረፁ ስራ አልተሰራም ነበር ብለዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለፀ ይህ ‹‹ሁሉንም የማቃመስ›› ሩጫ ቀድመው በተወሰኑ ዘርፎች ላይ የእራሳቸውን ጥሩ ነገር ይዘው ወጥተው የነበሩትን የማዳከም እና በየቦታው በቂ ግብአት የሌላቸው፣ ችግር የሚፈቱ ሳይሆን ችግር ውስጥ የተዘፈቁ ተቋማት እንዲኖሩን ምክንያት ነበር፡፡ ይሁን እና አሁን በልየታ ከፍተኛ ተቋማቱን በእራሳቸው የትኩረት አቅጣጫ ላይ እንዲተኩሩ መደረጉ በማደግና በመልማት ፀጋቸው ልክ የተሻሻሉ እና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ያስቻላል ብለዋል፡፡ እርሳቸው አክለውም በተለይ ዲላ ዩኒቨርሲቲም እንደ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በተሰጡት ትኩረቶች ላይ የበለጠ አቅሙን በማዋል ክህሎት ያላቸው፣ ከእራሳቸው አልፎ ህዝብና ሀገርን መለወጥ የሚችሉ ሙያተኞችን ማፍራት አለበት፤ የማህበረሰቡን ችግር በሚፈቱና ተተግባሪ በሆኑ ምርምሮች ላይ ማተኮር፣ የሰራተኞችን የስራ ተነሳሽነት ማሳደግ፣ መምህርኑን በአቅም ማብቃት እና በተቋሙ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ግንዛቤው እንዲኖራቸው መስራት ይኖርበታል፤ ለዚህ ደግሞ ቦርዱ እገዛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ በበኩላቸው በሚገባው ሁኔታ ስራዎች ተሰርተው ተቋሙን ለመለወጥ አመራሩና ሰራተኛው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልፀው ቦርዱም በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ሁሉ ያለተቆጠበ እገዛ ያደርጋል ብለው እንደሚምኑ ለቦርዱ አባላት ገልፀውላቸዋል፡፡ በውይይቱ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ አባላት ሁነው የተሰየሙት 1. ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር -ቦርድ ሰብሳቢ 2. ሙዐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ - አባል 3. ፕሮፌሰር አለማየሁ ጫላ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር - ም/ሰብሳቢ 4. ዶ/ር አዱኛ ደበላ የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር - አባል 5. ዶ/ር ፍቃዱ ጉሩሙ - አባል 6. ወ/ሮ ሳራ ይርጋ ከንግዱ ማህበረሰብ - አባል 7. አቶ አብዮት ደምሴ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ -አባል 8. ዶ/ር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የቦርዱ ፀሐፊ የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አካላትም የየዘርፋቸውን ሪፖርት ለውይይት አቅርበዋል።