ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከ ‘‘ቴክኖ ሰርቭ’’ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከ ‘‘ቴክኖ ሰርቭ’’ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ
ዲ.ዩ፦ ህዳር 17/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ ‘‘ቴክኖ ሰርቭ’’ ከተባለ የግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በቡና ልማት ዙርያ አብሮ ለመስራት የስምምነት ሰነድ መፈራረሙ ተገልጿል።
ዶ/ር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፤ አካባቢው እምቅ የቡና ሀብት ያለበት እንደመሆኑ መጠን ይህንን ለአከባቢው ማሕበረሰብ እና አገር እድገት ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው በሳይንሳዊ ምርምር ለመደገፍ ሰፊ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አክለውም በቡና ልማት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ የትምህርት መርሐ ግብር በመክፈት፣ የምርምር ማእከል በመቋቋም፣ የችግኝ ማፍያ ጣብያዎችን በማቋቋም፣ ለአከባቢው አርሶ አደሮች አገልግሎት እየሰጠን ነው ብለዋል።
ይህ በስፋት እና በጥራት ቡና እንዲመረት ዩኒቨርስቲው የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል። የዛሬው ስምምነትም በቡና ልማት ዙሪያ የምንሰራውን ስራ ደረጃውን ከፍ ለማድረግ ያግዘናል ሲሉ ተናግረዋል።
የ‘‘ቴክኖ ሰርቭ’’ ድርጅትን ወክለው የስምምነት ስነድ የፈረሙት ሚስተር ዴቪድ ፓርከር በበኩላቸው ድርጅታቸው በአሜሪካ መንግስት በኩል የግብርና ዘርፍን በተለያዩ ሀገራት የሚደገፍ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያም በቡና ልማት ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል። በዛሬው እለት የተደረገው ስምምነትም ዘመናዊ የቡና ምርምር ቤተሙከራ ለማደራጀት እንዲሁም ለቡና ምርት የሚጠቅሙ ግብአቶችን ለማሟላት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በአንፃሩ ዩኒቨርሲቲው ከሚሰራቸው የምርምር ስራዎች እና ከሚሰጣቸው የማሕበረሰብ አገልግሎቶች ውስጥ የቡና ልማት ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠነው መሆኑን ገልፀዋል።
ይህን አገልግሎት የበለጠ ተደራሽና ጥራት ያለው ለማድረግም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰፋፊ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ለዚህም ያግዝ ዘንድ ‘‘ቴክኖ ሰርቭ’’ ግብረ ሰናይ ድርጅት በቡና ልማት ዙሪያ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር አብሮ ለመስራት "ፈቃደኛ ስለሆነ እናመሰግናለን" ብለዋል ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ።