ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የሳይንስ ሳምንት መርሃግብር ተጠናቀቀ

ዲ.ዩ፦ ህዳር 16/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ስርፀት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት "ሳይንስ ለምግብ ዋስትና እና ሉአላዊነት" በሚል መሪ ሐሳብ ሲከናወን የቆየው አራተኛው የሳይንስ ሳምንት ፍጻሜውን አግኝቷል።
በመርሃግብሩ ወቅት ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ችሮታው አየለ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት በሀገራችን አመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞችንና ለም መሬት ይዘን የምግብ ዋስትናችንን ባለማረጋገጣችን ምክንያት በተጽእኖ ውስጥ እንድንወድቅ ሆነናል ብለዋል።
አያይዘውም ሀገሪቷ ያስተማረቻቸው ምሁራን በአገራችን ያለውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የተሻለ ስራ ለመስራት ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዲሁም ጥናቱን ወደ ተግባር መለወጥ ይጠበቅብናል ሲሉ አሳስበዋል።
ዶ/ር ችሮታው አክለውም ከምርምር ባለፈ ዩኒቨርሲቲው በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ አርባ ሰባት (47) ሄክታር የምርምር መሬት ወስዶ የስንዴ ምርት ለማምረት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል። ተባብረን፥ እጅ ለእጂ ተያይዘን ከሰራን ሀገራችንን ከልመና የምናወጣበት ጊዜ ሩቅ አይሆንምም ብለዋል።
በየአመቱ ህዳር ወር የምናከብረው የሳይንስ ሳምንት በትምህርት ስርዓቱ ላይ ተማሪዎች ለሳይንስ ትምህርት ያላቸውን ግንዛቤ አንዲጨምር ይረዳል ብለዋል።
በተጨማሪም ሳይንስ ለምግብ ዋስትናና ሉአላዊነት ያለውን ጠቀሜታ እንዲረዱ ያስችላል ያሉት ደግሞ ዶ/ር ደረጄ ክፍሌ የዲላ ዩኒቨረሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ኘሬዝዳንት ናቸው።
ዶ/ር ሀብታሙ ተመስገን የምርምር ስርፀት ዳሬክተር በበኩላቸው ተመራማሪዎች የምግብ ዋሰትናን ለማረጋገጥ ተተግባሪ ምርምሮችን አጽንኦት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
ዶ/ር ከበደ አበጋዝ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምግብ ሳይንስ ኒውትሬሽን ተመራማሪ በአንፃሩ ባለፉት ጊዚያት ጥናቶች ወደ መሬት ወርደዉ የህብረተሰቡን ችግር መፍታት ያልቻሉት መደማመጥና አብሮ መስራት ባለመኖሩ ነው ብለዋል።
አያይዘውም የሚኖሩንን ሳይንሳዊ ምርምሮች ከአከባቢው ማህበረሰብ ባህል፣ ልማድና አኗኗር ጋር በማሰናሰል የማህበረሰብን ዕውቀት በመጋራት የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉአላዊነት ማረጋገጥ ይቻላል ብለዋል።
ልዩ ልዩ ስራዎች እና ሀሳቦች የቀረቡበት አራተኛው የሳይንስ ሳምንትም ዛሬ ተጠናቋል።