ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተከብረ

ዲ.ዩ፦ ህዳር 27/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን "ሙስናን መታገል በተግባር" በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብሮ ውሏል። በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ ተከብሯል።
በዓሉን በንግግር የከፈቱት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) "አሁን ላይ እንደ ሀገር ሙስናን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በንቃት በመከታተል እና በመደገፍ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመታገል ግንባር ቀደም ተዋናይ ሊሆን ይገባል" ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው ከመንግስት መመሪያና ደንብ ውጪ በብዛት ይወጡ የነበሩ ወጪዎችን አሁን ላይ እንደ ተቋም ሙሉ በሙሉ እንዲስተካከሉ በማድረግ ብዙ ነገሮች ወደ መስመር እንደሚጡ መደረጉን ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ዲላ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ብቸኛ በመሆን በ2013 ዓ.ም በፌደራል ኦዲተር ግብረ-መልስ "የመጨረሻውን መልካም አስተያየት" እንዳገኘ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ታምሩ ተሾመ በበኩላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የፀረ-ሙስና ቀን ዓላማው የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ለፀረ-ሙስና ትግሉ በማነሳሳት ሙስናን በተግባር እና ትርጉም ባለው መንገድ እንዲታገል ለማድረግ ነው ብለዋል።
በፕሮግራሙ የስነ-ዜጋ እና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ያዕቆብ ጫቃ (ዶ/ር) የመወያየ ሰንድ አቅርበዋል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም በቀረበው ሰንድ መነሻነት ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ወቅት ሙስናና ብልሹ አሰራር ለሀገርም ሆነ ለተቋም እድገት ትልቅ እንቅፋት ከመሆናቸውም በላይ አሁን ላይ በሀገሪቱ የደህንነት፣ የፀጥታ እና የፖለቲካ መሳሪያ ጭምር እስከመሆን እየደረሱ መሆኑ ተብራርቷል። በመሆኑም ሁሉም በጋራ ሊከላከላቸው እንደሚገባ ከመድረኩ ተነስቷል።
በተጨማሪም በዓሉን አስመልክቶ የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ አሸናፊ ለሆኑ ተማሪዎች የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቷል።