ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዲላ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

ዲ.ዩ፦ ታህሳስ 11/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርትና ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክቶሬት ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀንን አከበረ። ቀኑ "አካታች የፈጠራ የስራና ሽግግራዊ መፍትሔ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት" በሚል መሪ ቃል በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ነው የተከበረው።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፍቃዱ ወ/ማርያም (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት "ይህ በዓል ከሌሎች በዓላት በተለየ ሰብዓዊነት ጎልቶ የሚታይበት እና የሚታወስበት ልዩ በዓል በመሆኑ ከሌሎች ቀናት ለየት ያደርገዋል" ብለዋል።
ዶ/ር ፍቃዱ አክለውም በዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው ትምህርታቸውን እንዲያጠናቅቁ አመርቂ ስራዎች ሲሰሩ መቆየቱን ገልጸዋል።
አያይዘውም በቀጣይ ዩኒቨርሲቲውን ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ ለማድረግ ተቋሙ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ቁርጠኛ ሆኖ እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው የልዩ ፍላጎት ትምህርትና ድጋፍ ማዕከል ዳይሬክተር አባቡ ተሾመ (ዶ/ር) በበኩላቸው በዓሉ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል (ECDD) ጋር በመተባበር እንደተዘጋጀ ገልጸዋል። በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ እንዲሁም በዲላ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ደግሞ በተከታታይነት ለ13ኛ ጊዜ መከበሩን አውስተዋል።
ዶ/ር አባቡ አክለውም በዓሉን በዓመት አንዴ አክብሮ ከመለያየት ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ እና የማስተማሪያ ስፍራ ለመፍጠር በተለይ የህንጻ አሰራር ምቹነት ላይ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
አቶ ለጋሱ ልዑልሰገድ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል /ECDD/ ፕሮግራም ዳይሬክተር በአንፃሩ አካል ጉዳተኞች አሁን ላይ ያሉበት ሁኔታ ከጉዳት አልባዎች ጋር ሲነፃጸር በብዙ መንገድ የተገለሉ በመሆናቸው እንደማንኛውም ዜጋ ከሁሉም አካላት እኩል ዕድል ሊያገኙ እንደሚገባ አሳስበዋል። በዚህ እረገድ መንግስት ቀዳሚ ኃላፊነቱን ሊይዝ እንደሚገባ አቶ ለጋሱ ተናግረዋል።
በፊላንድ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት 'Sini Tvuli suominen' በበኩላቸው አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ አቅም ኑሯቸው የሚገጥሟቸውንም ፈተናዎች መቋቋም እንዲችሉ ዩኒቨርሲቲው ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል (ECDD) ጋር እየሰራ ያለው ስራ የሚያስመሰግነው ነው ብለዋል።
ታምሩ እውነቱ (ዶ/ር) በ1990ዎቹ ጊዜያት በአፍሪካ ጭምር ተስማሚ ቴክኖሎጂን ለዐይነ ስውራን በማስተዋወቅ እና በማቋቋም የሚታወቁ የካናዳ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናቸው።
ዶ/ር ታምሩ በእለቱ አካል ጉዳተኞች ቴክኖሎጂን በመጠቀም በመማር ማስተማርም ሆነ በተመራማሪነት ብቁ ሆነው ወደ ተሻለ ሕይወት መሸጋገር የሚችሉበትን የረዥም ዓመት ልምድ እና ተሞክሮ ለተሳታፊዎች አካፍለዋል።
በበዓሉ ላይ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር አካላትን ጨምሮ የኮሌጅና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና ተማሪዎች ተሳትፈዋል ።
ዝግጅቱን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል በልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎች አድምቆታል።