ዲላ ዩኒቨርሲቲ በባዮጋዝ ግንባታና ማዕድን አለኝታ ጥናት ዘርፍ ከደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራረመ

ዲ.ዩ፦ ታህሳስ 07/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ በባዮጋዝ ግንባታና ማዕድን አለኝታ ጥናት ዘርፍ ከደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የደቡብ ክልል ማዕድን እና ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አጸደ አይዛ 15 ሚሊየን ብር በሆነ ወጪ በባዮጋዝ ግንባታና በማዕድን አለኝታ ጥናት ዘርፍ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የውል ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በምርምር እና በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
በክልሉ ከ6ሺ 300 በላይ ባዮ ጋዝ ግንባታ መካሔዱን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሯ በዚህም ከ31ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
ባለፈው አመት በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፍ የታየውን መልካም ልምድ በማስቀጠል ዘንድሮ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ላይ ትኩረት መደረጉንም ተናግረዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ ዩኒቨርሲቲው ከ2009 ዓም ጀምሮ በክልሉ የማዕድን አለኝታ ጥናት ሲያካሔድ የቆየ ሲሆን በዘርፉ ለበርካታ ወጣቶችም የስራ እድል ሲፈጥር መቆየቱን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአማራጭ ኢነርጂ እና በማዕድን አለኝታ ጥናት ላይ ትኩረት በማድረግ ከኤጀንሲው ጋር በትብብር ይሰራል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ የማህበረሰብ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማጎልበት ጥረት እንደሚደረግም አስረድተዋል።
አዲስ በሚጀመረው ፕሮጀክት በገጠር የመብራት አቅርቦት በሌለባቸው አካባቢዎች አማራጭ ኢነርጂ ማቅረብ እንዲሁም የማዕድን ዘርፉን በማጥናት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
ከአማራጭ ኢነርጂው በተጓዳኝ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከኤጀንሲው ጋር በትብብር ለመስራት የተፈራረመው የውል ስምምነት ፕሮጀክት በሚቀጥሉት 5 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን የክልሉ መንገስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃን ጠቅሶ የዘገበው የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ነው።