በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል የአጥንት ቀዶ ህክምና አገልግሎት በስፋት እየተሰጠ መሆኑ ተገለፀ

ዲ.ዩ፦ የካቲት 10/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ከትራፊክ አደጋ ጋር ተያይዞ ከሚሰጠው አገልግሎት መካከል በተለይ የአጥንት ቀዶ ህክምና አገልግሎትን በስፋት እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ዶ/ር አብይ ብርሃኑ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል በአጥንት ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት፤ የአጥንት ህክምና በብዛት ድንገተኛ ህክምና ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል። ይህም ድንገተኛ ህክምና ከአደጋ ጋር የተያያዙ ህክምና እና ካንሰርን ጨምሮ 'ኢንፌክሽን' እንዲሁም ሌሎች መሰል ህክምናዎች የሚሰጥበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አብይ አያይዘውም በአገራችን የትራፊክ አደጋ ከመንገድ ጥራት ችግር ጋር ተያይዞም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት እንደሚከሰት ገልፀዋል። እንዲሁም ወደ ገጠሩ አካባቢ ደግሞ መኪና የማይገባባቸው ቦታዎች እንደመኖራቸው መጠን የሞተር ብስክሌት እንቅስቃሴ ይበዛል ብለዋል።
የሞተር ብስክሌት ትራንስፖርት በባህሪው ለአደጋ የተጋለጠ በመሆኑ አብዛኛውን ጊዜ የምናሳልፈው በአደጋ ምክንያት የሚመጡ ስብራቶችን በማከም ነው ብለው ዶ/ር አብይ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ለተቋሙም ሆነ ለታካሚዎች ከፍተኛ ወጭ የሚያስከትሉ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ይህም ሲሆን የድንገተኛ አደጋዎች ህክምና ቅድሚያ የሚያስፈልጋቸው እንደመሆናቸው፣ የቀጠሮ ታካሚዎች ህክምና እንዲጓተትባቸው ጫና እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር እንግዳወርቅ ማሩ፣ በዩኒቨርሲቲ የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል የህክምና እና አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ በትራፊክ አደጋ በተለይ በሞተር ብስክሌት ምክንያት በሚደርሱ አደጋዎች ለሚከሰቱ ችግሮች ከሚሰጠው የህክምና አገልግሎት ውስጥ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
ጠቅላላ ሆስፒታሉ ሞያሌን ጨምሮ፣ የተወሰኑ የሶማሌ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂና የምስራቅ ጉጂ የተወሰኑ አካባቢዎች እንዲሁም አማሮ ቡርጂ ድረስ አገልግሎት እየሰጠ እንዳለ ዶ/ር እንግዳወርቅ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም የትራፊክ አደጋ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትል ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እንደ ተቋም የህክምና አገልግሎት አድማስ አስፍተን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በአጥንት ቀዶ ህክምና ክፍል የሚያገለግሉ ነርሶች አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው ተፈራ በበኩላቸው፤ አብዛኛውን ጊዜ የሚመጡ የህክምና ጉዳዮች በሞተር ብስክሌት እና በመኪና አደጋ የሚከሰቱ አደጋዎች ናቸው ብለዋል። ከድንገተኛ ህክምና ጀምሮ ለሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ለታካሚዎች የሚያስፈልጋቸውን እንክብካቤ እንሰጣለን ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥርና አደጋ መከላከል ዲቪዢን ኃላፊ ኮማንደር ታምሩ ሸጠኔ በበኩላቸው፤ የትራፊክ አደጋ ክስተት ነው፤ ክስተት ደግሞ በአጋጣሚ በድንገት የሚደርስ አደጋ ነው ብለዋል።
ኮማንደሩ አያይዘውም እንደ ይህ አደጋ በግማሽ ዓመት ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም እስከ ታህሳስ እና ጥር ወር 2015 ዓ.ም ድረስ "በዞናችን ጠቅላላ የአደጋ ብዛት በቁጥር 62 ሲሆን፤ ሞት ያስከተለው 35፣ ከባድ አደጋ 25፣ እና ቀላል አደጋ ደግሞ ሁለት" ነው ሲሉ በአሃዝ አስደግፈው ገልፀዋል።
እነዚህ አደጋዎች በሞተር ብስክሌት እና በመኪና ተለይተው ሲታዩ፤ በሞተር ብስክሌት 13 ሞት፣ ዘጠኝ ከባድ አንዲሁም አንድ ቀላል አደጋ፤ በአንፃሩ በመኪና 22 ሞት፣ ከባድ 16 እና አንድ ቀላል አደጋዎች ሁነው መመዝገባቸውን ኮማንደር ታምሩ አብራርተዋል።