በተቋማዊ የለውጥ ስራ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ክፍሎችና ሰራተኞች እውቅና ተሰጠ

ዲ.ዩ፦ የካቲት 18/2015 ዓም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል 'SBFR' (System Bottleneck Focused Reform) ተቋማዊ የለውጥ ስራ መተግበር ከጀምረ ወዲህ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ክፍሎችና ሰራተኞች እውቅና የመስጠት መርሃ-ግብር አካሂዷል።
ዶ/ር ምፅዋ ሩፎ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል ም/ኘሬዝዳንት፤
ላለፉት 13 ሳምንታት በጤና ሚኒስቴር እየተተገበረ ያለውን 'ሪፎርም' እንደተቋም ተቀብለን መተግበር ከጀመርን ጀምሮ ትልቅ ለውጥ ታይቷል ብለዋል።
በሀገሪቱ 'ሪፎርሙ' ከተተገበረባቸው 36 ሆስፒታሎች መካከል የዲላ ዩኒቨርስቲ አጠቃላይ ሆስፒታል ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘቱን አያይዘው ተናግረዋል ዶ/ር ምፅዋ።
ለዚህ ውጤት መገኘት ደግሞ የሰራተኞች ጠንክሮ መስራት ትልቁን ድርሻ ስለሚወስድ እስካሁን ለተመዘገበው ውጤት ሰራተኞችን ለማመስገን፣ ለቀጣይ ደግሞ የበለጠ ለውጤት እንዲሰሩ አደራ ለማለትም በማሰብ የተዘጋጀ የእውቅና መስጠት መርሃ-ግብር እንደሆነ ነው ዶ/ር ምፅዋ የገለፁት።
እርሳቸው አክለውም የሪፎርም አተገባበሩን በየክፍሎቻቸው በኃላፊነት የመሩት ኃላፊዎች ተቋምን የመምራት አቅማቸውን አሳይተውበታል ብለዋል። በአፈፃፀሙ ግንባር ቀደም የነበሩ የስራ ክፍሎችን እና ሰራተኞችን እውቅና በመስጠት የመስራትም ሆነ የመምራት አቅማቸውን የበለጠ ለማነሳሳት ይረዳል ብለዋል።
አጠቃላይ ሆስፒታሉ ወደ 'ሪፎርም' እንዲገባ ሲመረጥ የነበረበት ሁኔታ ጥሩ ያልነበረ ቢሆንም እንደታሰበው ተቋሙን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመለወጥ ውጤት ማየት ተችሏል ብለዋል። ይህም በቀጣይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ ተስፋ ሰጭ መሆኑ ከግንዛቤ ተወስዷል ነው ያሉት ም/ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ምፅዋ።
ዶ/ር ቢኒያም ወያ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል ህክምናና ስልጠና ዋና ዳሬክተር በበኩላቸው፤ ይህ የለውጥ ስርአት ትኩረት የሚያደርገው ለታካሚዎች የህክምና አሰጣጥን ማሻሻል ላይ እንዲሁም የህክምና ባለሙያውን ከታካሚው ጋር የሚኖረውን ግንኝነት ማሻሻል ላይ እንደሆነ ገልጸዋል።
አክለውም በዚህ ዘዴ ላይ የተለመዱ ችግሮችን ትኩረት ባደረገ መልኩ ሁልጊዜ በ24 ሰዓት ውስጥ የሚፈተሽ ስራን የመገምገም ሂደት ነውም ብለዋል። አሁን ላይ ያለው የተቋሙ ሰራተኛ ከጽዳት እስከ ከፍተኛ ሐኪም ድረስ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፉ መሆኑም ገልጸውልናል።
አቶ ትዝአለኝ ተስፋዬ፣ የዩኒቨርስቲው ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አጠቃላይ ሆስፒታል ማኔጂንግ ዳሬክተር በአንፃሩ፤ ለውጥ በቀላሉ የማይገኝ ይልቁንስ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ይህንንም ለሰራተኞች ግልፅ በማድረግ ለውጡ ተገልጋይን ማዕከል አድርጎ ጠንክሮ በመስራት የመጣ ነው ብቡዋል። አቶ ትዝአለኝ አያይዘውም ይህን ለውጥ ማስቀጠል የምንችለው ተገልጋዩን መሰረት አድርገን መስራት እስከቀጠልን ድረስ በመሆኑ ያሉብንን ክፍተቶች በሳይንሳዊ መንገድ በማረም የተገልጋይን ጥቅም በማስከበርና በማክበር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር አማኑኤል ዳንሳ፣ የ'ሪፎርሙ ፎካል ፐርሰን' እና የ'ኦኘሬሽን' ክፍል ዳሬክተር፤ ከዚህ በፊትም የነበሩን ባለሙያዎች እነዚሁ ነበሩ ነገር ግን አሁን ላይ 'SBFR' ሲመጣ ብዙ ለውጦች መምጣት መቻላቸውን አንስተዋል።
አክለውም በዚህ አሰራር የበለጠ በመትጋት ከዚህ የተሻለ መስራት እንደሚገባ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በየዘርፉ እውቅና ያገኙ የስራ ክፍሎች እና ሰራተኞች በተገኘው ውጤት መደሰታቸውን ገልፀው፤ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሰጠው እውቅና የበለጠ ተነሳሽነት እንደሚፈጥርላቸውም ተናግረዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን