በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለተመራቂ ተማሪዎች የሚሰጠውን የመውጫ ፈተና ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ውይይት ተካሄደ

ዲ.ዩ፦ የካቲት 22/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ጀምሮ ለሚመረቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ለመስጠት ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቃል። ይህን የመውጫ ፈተና ለማከናወን የሚረዱ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ሁኔታዎችን አስመልክቶ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ መንግስት እንደ ሀገር ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና ለመስጠት የተቋማቱ ዝግጅት ምን እንደሚመስል ምልከታ ለማድረግ የተለያዩ ቡድኖች መሰየማቸው ተገልጿል።
የመውጫ ፈተናውን ለመስጠት አስቻይ ሁኔታዎችን ዝግጁ ለማድረግ እና ከመንግስት የተቀመጠውን አቅጣጫ ለመተግበርና ለማሳካት እንደ ተቋም እስከ ትምህርት ክፍሎች ድረስ ተወርዶ እየተሰራ እንደሆነ ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
ዶ/ር ችሮታው አያይዘውም ኮሌጆች እና የትምህርት ክፍሎች እንደ ተቋም ያሉትን ውስንነቶች ተቋቁመው ተማሪዎች ተመዝነው በብቃት እንዲያልፉ ለማስቻል በቁርጠኝነት እየሰሩ ነው ብለዋል። ተማሪዎች በትጋት እንዲያጠኑ፣ መምህራን በተገቢው ሁኔታ ትምህርቶችን እንዲሸፍኑ ጥሩ ስራ እየተሰራ ቢሆንም፥ ከፍተኛ የግብዓት እጥረት እና የግዥ ስርዓት መጓተት በሚሰሩ ስራዎች ላይ ማነቆ እንደሆነ ዶ/ር ችሮታው ጠቁመዋል።
ከትምህርት ሚኒስቴር መጥተው ዩኒቨርሲቲው ፈተናውን ለመስጠት እያካሄደ ያለውን ዝግጅት ከገመገሙት ባለሙያዎች መካከል አቶ ጫኔ አደፍርስ በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ያለው ዝግጅት መልካም የሚባል መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።
አቶ ጫኔ አክለውም የመውጫ ፈተናው በተሳካ ሁኔታ መሰጥት እና የሚገኘው ውጤት የተሻለ ትውልድ ለማፍራት፥ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሁነው በሙያቸው የሚኮሩ ምሩቃንን ለማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
አያይዘውም እርሳቸውና ልዑካቸው በዲላ ዩኒቨርሲቲ ቅድመ ዝግጅት ዙሪያ ባካሄዱት ምልከታ ብዙ ጠንካራ ስራዎችን ማየታቸውን ጠቅሰው በተለይ የተፈጠሩ የኮሚቴ አደረጃጀቶች፣ የአመራሩን ቁርጠኝነት አመላካች ውሳኔዎችን ለአብነት አንስተዋል።
ይሁን እንጅ ለተማሪዎች የሚሰጡ የማጠናከሪያ ትምህርቶች፣ ተማሪዎች በሚገባው ልክ የፈተናውን አስፈላጊነት እና አይቀሬነት ተገንዝበው ወደ ተግባር ጥናት እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች በቶሎ ተጠናክረው መሰራት አለባቸውም ብለዋል። ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችሉ የተጓደሉ ግብአቶችን የማሟላት ስራዎችም በትኩረት መሰራት አለባቸው ነው ያሉት አቶ ጫኔ።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ለፈተናው መሳካት "በሙሉ ትኩረታችን በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት የመጀመሪያ ቀን አንስቶ ወደ ስራ እንገባለን" ብለዋል። ዶ/ር ችሮታው አክለውም ፈተናው በስኬት ለመፈፀም ከማጠናከሪያ ትምህርት፣ ከፈተና ማውጣት እና ሌሎች ተግባራት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች በትኩረት እየታዩ ይፈታሉ ነው ያሉት።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች በመውጫ ፈተናው አጠቃላይ ዝግጅት፣ አስፈላጊ ግብአት እና አተገባባር ዙሪያ ሐሳብ፣ አስተያየትና ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በተነሱት ሀሳቦች ዙሪያ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) እንዲሁም ከትምህርት ሚኒስቴር የመጡት ባለሙያዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን እንደ ተቋም የሚታዩ ጉዳዮች እና ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ተወስደው ግብአት የሚደረጉ አንዳንድ ሀሳቦች ተለይተው ይታያሉ ተብሏል። በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው አመራር አካላት እና የካውንስል ጉባኤ አባላት ተሳታፊ ሁነዋል።
የመውጫ ፈተናውም በኮምፒውተር ስርአት በ'ኦንላየን" የሚሰጥ መሆኑ በመድረኩ ተብራርቷል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን