ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን (March 8) በመላው ዓለም እየተከበረ ነው

ዲ.ዩ፦ የካቲት 29/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት በዓለምአቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ለ47ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን ዓለምአቀፍ የሴቶት ቀን አስመልክቶ ተከታዩን መልዕክት ያስተላልፋል።
#ለማርች8 (March8) ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን የዚህ ዓመት መሪ ቃል፦
"ፈጠራና ቴክኖሎጂ ለፆታ እኩልነት" ፤
1) ማርች 8 ዓለምአቀፍ የሴቶችተ ቀን ታሪካዊ አመጣጥ፥
ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን እንዲከበር ከመወሰኑ በፊት በተለያዩ ሀገሮች ይከበር አንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ፡፡ የበዓሉን ታሪካዊ አመጣጥ ስንመለከት እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1908 ከግዛት መስፋፋትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙት ጭቆናዎች እየተባባሱ ሄዱ፡፡
ይህ ጭቆና የራዲካል ፌሜኒስት አስተሳሰብ እንዲወለድና ሴቶች ለለውጥ እንዲነሳሱ ጋበዙ፡፡ በዚሁ አመት 1500 የሚሆኑ ሴቶች የስራ ሰዓት እንዲቀነስላቸው የተሻሻለ የጉልበት ክፍያ እንዲኖርና የመመረጥና የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር በሰላማዊ ሰልፍና በተለያዩ መንገዶች መጠየቅ ጀመሩ፡፡
በመቀጠልም በ1909 የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ በዓሉ በፌብራሩዋሪ 28 በሁሉም የአሜሪካ ግዛቶች እንዲከበር ድንጋጌ አወጣ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በዓሉ በአሜሪካ በየአመቱ የመጨረሻ አሁድ ይከበር ጀመር፡፡
በ1910 በስፔን ሀገር የተካሄደው አለም አቀፍ የሶሻሊስት ስብሰባ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የሚከበርበትን ዕለት አስመልክቶ ውሳኔው 17 ሀገሮች ባሉበት የሴቶች መብት ንቅናቄ ድጋፍ አገኘ፡፡
በስፔን ሀገር ጉባኤ ላይ በተወሰነው መሠረት በዓሉ በ1911 ለመጀመሪያ ጊዜ ማርች 19 በኦስትሪያ፣ በዴንማርክ፣ በጀርመንና በስዊዘርላንድ አንድ ሚሊዮን ሴቶችና ወንዶች በተገኙበት በሰላማዊ ሰልፍና በዕግር ጉዞ ተከበረ፡፡
የዚህ ሰልፍና ጉዞ አላማ የመመረጥና የመምረጥ፣ እንዲሁም በመንግስት ሥራ አኩል የመቀጠር መብት እንዲከበርና ለሴቶች የሙያ ስልጠና እንዲሰጥና በስራ ላይ የሚታየው ፆታዊ መድልኦ እንዲቆም ለመጠየቅ ነበር፡፡ ከዚህ አመት በኋላ በዓሉ በብዙ የአሜሪካ፣ የምስራቅና የምዕራብ አውሮፓ ሀገሮች በድምቀት ይከበር ጀመር፡፡
2) ማርች 8 ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን ለምን ይከበራል?
በዓሉ የሚከበርበት ዋና አላማ በዓለም ላይ ያሉ መንግስታት የሴቶች ጉዳይ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጉዳይ እንደሆነ አምነው በመቀበል በሴቶች ዙሪያ ፖሊሲዎቻቸውን አሰራሮቻቸውን በመፈተሽ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ መድልዎችን እንዲያስወግዱና የሴቶች ተጠቃሚነትና ተሳታፊነትን እንዲያረጋግጡ ለማነሳሳት ነው፡፡
በዓሉ የሚከበርበት ሌላኛው ዋነኛ ምክንያት በዓለም ላይ ያሉ ሴቶች በድንበር፣ በሀይማኖት፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በባህል ወዘተ ሳይለያዩ የሚደርስባቸውን ጭቆናና መድልኦ የሚያወግዙበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ድምፃቸውን በጋራ የሚያሰሙበት፣ ለነፃነት፣ ለፍትህ ለዕኩልነት ያደርጉትን ተጋድሎ የሚዘክሩበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበት፣ ለበለጠ ትግል ተቀናጅተው ለመንቀሳቀስ ቃል የሚገቡበት ነው፡፡
3) ማርች 8 በሀገራችን መከበር የጀመረው መቼ ነው? በዓሉን ማክበር ለምን አስፈለገ?
ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በሀገራችን መከበር የተጀመረው በ1968 ዓ.ም ሲሆን በዓሉ ዘንድሮ ”ፈጠራና ቴክኖሎጂ ለፆታ እኩልነት’’ (Digital: Innovation and Technology for Gender Equality) በሚል መሪ ቃል በአለምአቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ በሐገራችን ኢትዮጵያ ለ47ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡
የማርች 8 ቀን አስመልክቶ በዓልን ስናከብር ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አገር አቀፍ እና አለም አቀፍ ስምምነቶችን በማስታወስ የኢትዮጵያ ሴቶች ይህን በዓል ሲያከብሩ ከአለም ሴቶች ጋር ያላቸውን የትግል አንድነት ከማጠናከር የዘለለ የራሳቸው ታሪካዊ ምክንያት አላቸው፡፡
የሀገራችን ሴቶች ከአጋር ወንድሞቻቸው ጋር በመቀናጀት የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚያስተውሉበትና ሰማዕታት የሚዘከሩበት ዕለት ነው፡፡
ዕለቱ የሀገራችን ሴቶች በህገ-መንግስቱና በሌሎች ህጐች የተረጋገጡላቸውን መብቶች ለማስከበር የትግል አንድነታቸውን የሚያሳዩበት፣እንዲሁም በሀገሪቷ በሚካሄደው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በተናጠልም ሆነ በመደራጀት ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለመሆን ትግላቸውን የሚያጠናክሩበት ነው፡፡
(Digital: Innovation and Technology for Gender Equality)
”ፈጠራና ቴክኖሎጂ ለፆታ እኩልነት’’
ለዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን
እንኳን አደረሳችሁ
የሴ/ህ/ወ/ጉ ዳይሬክቶሬት
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የካቲት 29/2015 ዓ.ም