በምርምር የበለፀገ የምርጥ ዘር ድንች ለሞዴል አርሶ አደሮች ተሰራጨ

ዲ.ዩ፦ መጋቢት 01/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በቡሌ ወረዳ ለተመረጡ አርሶ አደሮች በምርምር የበለፀገ የምርጥ ዘር ድንች አሰራጭቷል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፤ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየር በማሰብ የተለያዩ ስራዎች ከዞኑ ጋር እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል። ዛሬም ለተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ድንች በማሰራጨትና ዘሩን እንዲባዛ በማድረግ ለቀረው አርሶ አደር እንዲዳረስ የማድረግ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
ደረጀ ክፍሌ (ዶ/ር) የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም በርከት ያሉ ለማህበረሰብ ግልጋሎት ተደራሽ የሆኑ ኘሮጀክቶችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በቡሌ ወረዳ በዋናነት በቀርቀሃ፣ አኘል፣ እንሰት እንዲሁም ድንች ልማት ላይ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አንስተዋል።
አያይዘውም እነዚህ ኘሮጀክቶችን እንደ መልካም ጅምር በመውሰድና አጠንክሮ በመቀጠል ከህብረተሰብ ለሚነሱ ጥያቀዎች በጥናትና ምርምር በመታገዝ የመፍትሄ ሰጭነት ሚናችንን ከፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ብለዋል።
በሌላ በኩል አቶ ተካልኝ ታደሰ፣ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳሬክተር፤ ምርምር በምናከናውንባቸው አከባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች የምርምር ውጤት የሆኑ ዝርያዎችን በማደል ምርቱን እንዲያስፋፉና ለሌሎች አርሶ አደሮች የእውቀት ሽግግር በማድረግ እርስ በእርስ የሚማማሩበትን መንገድ ለመፍጠር እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ዙር የተሰራጨው ምርጥ ዘር ለተመረጡ አርባ (40) አርሶ አደሮች ሲሆን በምረት ወቅት ዘሩን ለሌሎች አርሶ አደሮች እንዲያዳርሱ ስምምነት ላይ መደረሱንም አቶ ተካልኝ አሳውቀዋል።
ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) የጌዴኦ ዞን ም/አስተዳዳርና የግብርና መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው፤ ከሌሎች ስራዎቹ በተጨማሪ በማህበረሰብ አገልግሎት እረገድ ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየሰራ ያለው ስራ ጥቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
አቶ በራቆ በራሶ፣ የቡሌ ወረዳ አስተዳደር በበኩላቸው፤ በወረዳው ያሉ አርሶ አደሮች ከፍተኛ የገቢ ምንጫቸው የድንች ምርት እንደመሆኑ መጠን በጥያቄአችን መሰረት ባደረጋችሁት ጥናትና ምርምር ይህ የምርጥ ዘር ድንች የአካባቢውን አርሶ አደር ኑሮ እንደሚያሻሽል እምነታችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የምርጥ ዘር ጥናትና ምርምር አስተባባርዎች የሆኑት አቶ ንጉሱ ደበበ እና አቶ አብዲ አደም በበኩላቸው፤ ዛሬ ለስርጭት የበቃው ምርጥ ዘር ዲንች "በለጡ" የተሰኘው ዝርያ ሲሆን ለ40 አርሶ አደሮች አንድ አንድ ኩንታል ዘር በጥቅሉ 40 ኩንታል መሰጠቱን ተናግረዋል። ሌሎች አስር ( 10) ያህል የድንች ዝርያዎች አሁን ላይ ጥናት እየተደረገባቸው መሆናቸውን እና ጥናቱ ሲጠናቀቅ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጩ አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።
የዚህ የምርጥ ድንች ዝርያ ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶ አደሮች መካከል አቶ መስፍን ክፍሌ እና አብርሃም ተስፍዬ በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርስቲ ይህንን ድጋፍ በማድረጉና የእድሉ ተጠቃሚ በመሆቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀው እነርሱም ተሞክሮውን ለሌሎች አርሶ አደሮች እንደሚያጋሩ ተናግረዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን