ዲላ ዩኒቨርሲቲ በኪነ-ህንፃ ምህንድስና፣ በህክምና እና በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

ዲ.ዩ፦ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በቴክኖሎጂና ምህንድስና ኮሌጅ ስር በኪነ-ህንፃ ምህንድስና (አርክቴክቸር) ትምህርት ክፍል፣ በህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በህክምና (ሜዲሲን) ትምህርት ክፍል እንዲሁም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመርቋል።
ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ፤ ለተመራቂ ተማሪዎች፣ ለተመራቂ ወላጆች እንዲሁም ለተማሪዎቹ ለምረቃ መብቃት በተለያየ መልኩ ለተጉ ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ማቴዎስ አክለውም "የዘንድሮ ተመራቂዎች ከትምህርት እና ፈተና ባለፈ በዓለምአቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጫናዎች ተቋቁማችሁ ለዚህ የበቃችሁ በመሆናችሁ በእራሳችሁ ልትኮሩ ይገባል" ብለዋል።
ተመራቂዎች ምንም እንኳ ከተቋሙ ተመርቀው ቢወጡም በዩኒቨርሲቲው አሉምናይ በኩል ቤተሰባዊ ግንኙነቱ እንደሚቀጥል የገለፁት ዶ/ር ማቴዎስ፥ በቀጣይ ተመራቂዎች በሚሰማሩበት መስክ ሁሉ አምባሳደር ሁነው የዩኒቨርሲቲውን መልካም ስም እንዲያስቀጥሉ የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራርና አሉምናይ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ይልማ በበኩላቸው፤ በዛሬው እለት በድህረ-ምረቃ መርሃ-ግብር 68 ወንድ እና ዘጠኝ (9) ሴት በድምሩ 77፣ በመደበኛው መርሃ-ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ 64 ወንድ እና 24 ሴት በድምሩ 88፣ በተከታታይ የትምህርት መርሃ-ግብር 117 ወንድ እና 30 ሴት በድምሩ 147፣ በአጠቃላይ 249 ወንድ እና 63 ሴት በድምሩ 312 ተመራቂዎች ለምርቃት መብቃታቸውን አብስረዋል።
በዕለቱ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህክምና ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነው ዶ/ር ብርሃን አዳነ አጠቃላይ ውጤት 3.86 ነጥብ በማስመዝገብ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
የማዕረግ ተመራቂው ዶ/ር ብርሃን አዳነ "ከምንም በላይ ፈጣሪዬ ለዚህ ክብር እንድበቃ ስላደረገኝ ክብር ይግባው" ሲል በስኬቱ መደሰቱን ገልጿል።
የምርቃት ስነ-ስርአቱ የህክምና ተመራቂዎች ሙያዊ ቃለ-ምሃላ በመፈፀም የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በስነ-ስርአቱ የክብር እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር አባላት እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። የዲላ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከልም ልዩ ልዩ ጣዕመ ዜማዎችን በማቅረብ ዝግጅቱን አድምቆታል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ