ለዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በሁለንተናዊ ለውጥ አመራር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ

ዲ.ዩ፦ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሰው ሀብት ልማት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬትና ተቋማዊ ለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በጋራ በመሆን ለበላይ አመራሮች፣ ዳይሬክተሮች፣ ዲኖች እና ቡድን መሪዎች ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሁለንተናዊ ለውጥ አመራር (Trasnformational Leadership) ዙሪያ ስልጠና ሰጥተዋል።
ዳዊት ሃይሶ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአስ/ተማ/አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት፤ የተቋምን ስኬት በውጤታማነት ከግብ ለማድረስ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንዱ የአመራርን አቅም መገንባት ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል። ከዚህም አኳያ አመራሮች በትምህርትና በስራ የቀሰሙትን ልምድ ከተቋሙ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለዚህም ይረዳ ዘንድ መሰል ስልጠናዎችን በመስጠት አቅም የሚገነባበት ሁኔታ መፍጠር ይገባል ያሉት ዶ/ር ዳዊት፥ አሁን የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና ወደ ስራ መለወጥ እንዲቻልና ለተቋሙ "ትራንስፎርሜሽን" አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ድጋፍና ክትትል ይደረጋል ብለዋል፡፡
አቶ ይመኑ ዳካ፣ በዩኒቨርሲቲው የተቋማዊ ለውጥ አመራርና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ የሁለንተናዊ ለውጥ አመራር የአቅም ግንባታ ስልጠናው አሁን አገሪቱ ከምትፈልገው የዕድገት ደረጃ አንፃር አመራሩ ሰልጥኖ መምራት አለበት በሚል መነሻ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከስልጠናው በርካታ ግብአቶችን እንደምናገኝ በማሰብ ወደ ተግባር ገብተናል ያሉት አቶ ይመኑ፥ ስልጠናውን የወሰዱ መሪዎች በስራቸው ለሚገኙ ባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰጡ በማድረግ በሂደት በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች ሁሉ ይህንን ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የስኳር ኢንዱስትሪ ግሩፕ የሥራ አመራር ስልጠና ኃላፊ እና ከፍተኛ አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ኮስትር ቸኮል በበኩላቸው፤ የስልጠናው ዓላማ ዩኒቨርሲቲው በለውጥ ሂደት ላይ ያለ በመሆኑ አዳዲስ ሃሳቦች ስለሚያስፈልጉት ነው፤ ለዚህም ሁለንተናዊ ለውጥ አመራርነት የሰው አሰራርን እና የተቋም የአሰራር ስርአትን የመቀየር ሃሳብ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ ወርቅአገኘሁ በፈቃዱ በኦዳኣያ ግቢ ማኔጂንግ ዳይሬክተር እና ወ/ሮ አለም ብርሃኑ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሰጡን አስተያየት፤ ስልጠናው ያላቸውን ዕውቀት እና ክህሎት እንዲያዳብሩ የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ሰልጣኞቹ አክለውም ስልጠናው ለሁሉም ፈፃሚ ሠራተኞች ተደራሽ የሚሆንበት ሁኔታ ቢመቻች የተሻለ አቅም በመገንባት የተሻለ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለውናል።
በስልጠናው ማጠናቀቂያ ንግግር ያደረጉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ዮናስ ሰንዳባ በበኩላቸው፤ ሁሉም መሪ ነው የሚለውን እሳቤ ይዘን በስልጠናው የተሻለ አቅም በመገንባት የተሻለ ለውጥ እንደሚመጣ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።
ዶ/ር ዮናስ አክለውም ስልጠናውን ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ እና የሚገኙ ክህሎቶችን በማዳበር ወደ ስራ እንገባለን ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው መሰል ለውጥ የሚፈጥሩ ስልጠናዎችን በቀጣይነት እና ተከታታይነት ባለው መልኩ እንደሚያዘጋጅ ዶ/ር ዮናስ ሰንዳባ ገልፀዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ