በጣሊያን ቱሪን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከኢትዮጵያ ኤምባሲ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

ዲ.ዩ፦ መጋቢት 06/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በተማሪዎች የልውውጥ ፕሮግራም በጣሊያን ሀገር ቱሪን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በሀገሪቱ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
በቱሪን ዩኒቨርሲቲ ለስድስት ወራት ልምድ ለመለዋወጥ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ የሄዱት ስድስቱ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በቱሪን ከተማ በሚገኘው በጣሊያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንስላ ፅ/ቤት ነው ውይይቱን ያደረጉት።
በውይይቱ የኤምባሲው ምክትል ሚሲዮን አቶ አሰፋ አብዩ እና አቶ ደሳለኝ መኮንን የተገኙ ሲሆን ከአምባሳደር ደሚቱ አምቢሳ ለተማሪዎቹ የተላከ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክትን አድርሰዋል።
ተማሪዎቹ ለምክትል ሚሲዮኖቹ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የትኩረት አቅጣጫዎችን አብራርተዋል። ተማሪዎቹ አክለውም ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሰራቸው ያሉ የዱመርሶ የቡና ምርምር፣ የሰመሮ ጋምቤላ የአፈር ጥበቃና ደን ልማት፣ የቡሌ ቀርከሃ ልማት፣ የእፅዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ፕሮጀክቶችን አስተዋውቀዋል።
በውይይቱ ዩኒቨርሲቲው የከፈታቸው የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት መርሃግብሮችም ትውውቅ የተደረገባቸው ሲሆን ተማሪዎቹ በጣሊያን ሀገር ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነቶችን ለመመስረት ኤምባሲው የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
ምክትል ሚሲዮኖቹ በበኩላቸው ኤምባሲው በጣሊያን ሀገር የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር አብረው እንዲሰሩ የማግባባት ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ መሰል ግንኙነቶችን ለመመስረት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝም ኤምባሲው ዝግጁ ነው ብለዋል።
"ኢራስመስ ፕላስ" የተሰኘው ፕሮግራም በዲላ ዩኒቨርሲቲ እና ቱሪን ዩኒቨርሲቲ የሚተገበር ሲሆን ተማሪዎች እና መምህራን ለተጨማሪ እውቀትና ልምድ ልውውጥ ወደ ተቋማቱ ይጓዛሉ።
መረጃውን ከጣሊያኑ ቱሪን ዩኒቨርሲቲ የላከልን የፕሮግራሙ ተሳታፊና በ'Multiculturalism and Governance' የትምህርት መስክ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆነው መምህር ሔኖክ ንጉሴ ነው።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ