ዓለማቀፉ የሴቶች ቀን "ማርች 8"ን ተንተርሶ በ"እናት" መፅሐፍ ላይ ህዝባዊ ውይይት ተካሄደ

ዲ.ዩ መጋቢት 8/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርስቲ "ማርች 8" የሴቶች ቀን በዓለምአቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ “ፈጠራና ቴክኖሎጂ ለጾታ እኩልነት” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል።
በእለቱም ጭብጡን ሴትነትን ከቤተሰብ ህይወት እስከ ማህበረሰባዊ ሁለንተናዊ ጉዳዮች በይኖ የሚዳስስ "እናት" የተሰኘ መፅሐፍ ተመርቆ ለውይይት ቀርቧል። መፅሐፉን በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶ/ር ይሁኔ አየለ ናቸው የፃፉት።
በመድረኩ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትን ወክለው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ዳዊት ሀዬሶ (ዶ/ር) የአስ/ተማ/አገ/ምክትል ፕሬዝዳንት፤ የሴቶች ትግል ከጥንት ጀምሮ እየተቀጣጠለ እየጨመረ የመጣ ነው ብለዋል።
የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አጀንዳ አድርገው የሚደረጉ ትግሎች የሴቶችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ሰፊ የሆኑ ክፍተቶች በመኖራቸው በአጠቃላይ አውሮፓና አሜሪካ ሰፊ ንቅናቄ መፍጠሩን በታሪክ ማየት እንደሚቻል ገልፀዋል።
ዶ/ር ዳዊት በንግግራቸው የሴቶች ቀን ዛሬ ከሚከበርበት መሪ ሐሳብ አንጻር በተለይ በገጠሪቱ የአገራችን ክፍል የሚኖሩ ሴቶችን በቴክኖሎጂ ድጋፍ ኑሯቸውን ማቅለል እንዲቻል በሰፊው መሰራት እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዓለም ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ማርች 8 የአንድ ቀን በዓል ብቻ መሆን የለበትም ብለዋል። ወ/ሮ ዓለም እንዳሉት መንግስታት የሴቶችን መብት በማስጠበቅ የፈረሙትንና የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ሰብአዊ ጥሰቶች፣ ጥቃቶች እንዲቆሙ ከአቻ ወንድሞቻቸው ጋር በመቆም ዘወትር የሚተገበር ተግባር ነው።
በመድረኩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ጉዳዮች በጥልቀት በተነተነው እና በይሁኔ አየለ (ዶ/ር) በተፃፈው "እናት" መጽሐፍ ላይ ዳሰሳና ወይይት የደረገውም በሴቶች ህይወት ላይ የተፈጠሩ ስንክሳሮችን በእውቀት ለመፍታት መሆኑ ተገልጿል።
በዲላ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ምስራቅ ጠና ከስርአተ ጾታ እና የስነ ጽሁፍ መምህሩ ቴዎድሮስ ቦጋለ ደግሞ ከቋንቋና ስነ-ፅሁፋዊ አውዶች አንፃር በመፅሐፉ ላይ ዳሰሳ አቅርበዋል።
ሁለቱም አቅራቢዎች የመጽሐፉን አስፈላጊነት እንዲሁም ኪናዊ ለዛ በተመለከተ ጠለቅ ያለ ሙያዊ እይታቸውን አጋርተዋል። ዳሰሳውን ተከትሎ ከታዳምያን ተጨማሪ ሀሳቦች እና ጥያቄዎች ተነስተው ከመጽሐፉ ደራሲ ግብረ መልሶች ተሰጥቶባቸዋል።
መፅሐፉ ከደራሲው የፅሁፍ ስራ አንስቶ እስከ ህትመትና ሽያጭ ድረስ በተለየ ሁኔታ ያለፈበትን ሄድ በተመለከተ የአማርኛ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ መምህሩ ዘላለም ጌታቸው (ዶ/ር) አጭር ማብራሪያ ለታዳሚያን አክፍላዋል።
ዶ/ር ዘላለም አክለውም መፅሐፉ በእናቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ "እናት ለማህበረሰብ ልማት" የሚል ግብረ-ሰናይ ድርጅት እንዲመሰረት ምክንያት ሁኗል ብለዋል። የመጽሐፉ ሽያጭ ገቢም ሙሉ በሙሉ ለዚሁ ድርጅት ስራዎች እንደሚውል ተገልጿል።
መድረኩን በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት እና ህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ያዘጋጁት ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎች፣ መምሀራን እና ተማሪዎች ታድመውታል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ