"በዩኒቨርሲቲያችን የመውጫ ፈተናን በአግባቡ ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ነው"

ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር)
የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ተወካይ
ዲ.ዩ፦ መጋቢት 8/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ከያዝነው 2015 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስትና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ የታቀደውን የመውጫ ፈተና (Exit exam) ዲላ ዩኒቨርስቲ ለተመራቂ ተማሪዎቹ በ"ኦንላይን" ለመስጠት የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ማቴዎስ ሀብቴ (ዶ/ር) የዲላ ዩኒቨርስቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ፤ መንግስት ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ በማሰብ በመጪው ሐምሌ ወር በመንግስት እና በግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ እቅድ የያዘለትን የመውጫ ፈተና ዩኒቨርሲቲው በብቃት ለመስጠት ሰፊ የዝግጅት ስራዎች እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለስራው መሳካት በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የሚመራ ዋና ግብረ ኃይል እና በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት የሚመራ ንዑስ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል። ግብረ ኃይሎቹም የመውጫ ፈተናውን በአግባቡ ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎችን ከወዲሁ እየሰሩ መሆኑን ነው ዶ/ር ማቴዎስ የገለፁት።
የትምህርት ክፍሎች ኃላፊነት ወስደው ለተማሪዎች እና መምህራን ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዎችን በስፋት ሲሰሩ መቆየታቸውን ያወሱት ዶ/ር ማቴዎስ፣ የመውጫ ፈተናን የመስጠት ልምድ የነበራቸው የህግ እና ጤና ሳይንስ ኮሌጆች ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ መደረጉንም ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር ማቴዎስ ገለፃ፤ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት በወሰነው የማጠናከሪያ ትምህርት የሰዓት ማዕቀፍ መሠረት ወደ ድርጊት መርሃ ግብር ይገባል። በዚህ ማዕቀፍ መሰረትም በሁሉም ትምህርት ክፍሎች ለሚፈተኑ ተማሪዎች በማታ እንዲሁም ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ለመውጫ ፈተና የተመረጡ "ኮርሶች" የክለሳ ትምህርት መሰጠት ይጀምራል።
ለዚህም በየትምህርት ክፍሉ ያሉ የዩኒቨርሲቲው መምህራን የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት የማጠናከሪያ ትምህርት ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸው ታውቋል።
ከማጠናከሪያ ትምህርቱ ጎን ለጎን በዩኒቨርሲቲው የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል ባለሙያዎች በኩል ፈተናውን በ"ኦንላየን" ለመውሰድ የሚያስችል የኮሚውተር ስርአት አጠቃቀም ስልጠና ለተፈታኝ ተማሪዎች የሚሰጡ ሲሆን፥ ስልጠናው ተፈታኞች ከወዲሁ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና የፈተና ስርአቱን እንዲላመዱ ያስችላቸዋል ነው የተባለው።
ከስልጠናው በኃላ ዋናውን ፈተና ለመውሰድ አቅም የሚፈጥር የሞዴል ፈተና ተዘጋጅቶ በ"ኦላይን" ስርአት እንዲፈተኑ እንደሚደረግም የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ተወካዩ ገልፀዋል።
ፈተናውን ለመስጠት የሚያስችል የግብአት አቅርቦት ጋር በተገናኘ ዶ/ር ማቴዎስ ሲያብራሩ፤ አሁን ላይ ለተማሪዎች የመውጫ ፈተናን ለመስጠት የሚያስፈልጉ አብዛኞቹ ዝግጅቶች በበቂ ሁኔታ እየተሟሉ ነው ብለዋል።
ተማሪዎችን ለፈተናው ብቁ አድርጎ ፈተናውን በስኬት ለመፈፀም የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ከአሁን አንስቶ እስከ ፈተናው ማጠናቀቂያ ድረስ በትኩረትና ትብብር እንዲሰሩ ዶ/ር ማቴዎስ ሀብቴ ጥሪ አቅርበዋል።
በያዝነው አመት ዲላ ዩኒቨርሲቲ በ29 የትምህርት ክፍሎች ከ5200 በላይ ተማሪዎችን በመውጫ ፈተና እንደሚያስፈትን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን