የሴቶችን የምርምርና አመራርነት ተሳትፎ ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ

ዲ.ዩ፦ መጋቢት 16/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ከNORHED ll ReRED ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የሴቶችን የተቀናጀ የምርምርና አመራርነት አቅም ለማሳደግ ያለመ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ከእንግሊዝ ሀገር ካርዲፍ ዩኒቨርሲቲ (Cardiff University) የመጡት ፕሮፌሰር አሊሰን ብራውን የሴቶችን የተቀናጀ የምርምርና አመራርነት ተሳትፎ ማጎልበት (Enhancing Women's participation in collaborative Research and Academic leadership) በሚል ርዕሰ ገለጻ አቅርበዋል።
ፕሮፌሰሯ በገለጻቸው እስከዛሬ በህይወት እና ሙያ መስካቸው ያካበቷቸውን ልምዶችና እውቀቶች ለመድረኩ ተሳታፊዎች አካፍለዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንት ደረጀ ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር፤ እንደሀገር በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ዲላ ዩኒቨርሲቲ በ'አፕላይድ' ሳይንስ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ሀይል ማፍራት አንዱ ተልዕኮው ነው ብለዋል።
ይህንን ዓላማ ለማሳካትም ሴት መምህራን በጥናትና ምርምር የበኩላቸውን ሚና እንዲያበረክቱ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዶ/ር ደረጀ የገለፁት።
በምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት የምርምር አቅም ግንባታና ጉድኝት አስተባባሪ አቶ አሸናፊ አስራት በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም ከኖርዌይ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሴት ተመራማሪዎች ተሳትፎና ብቃት ከፍ ለማድረግ በፕሮጀክቱ አንደኛው ዙር የተከናወኑ ስራዎች መኖራቸውን አውስተዋል።
ከአንደኛው ዙር የተገኙ ስኬቶችና እድሎች እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በየኮሌጆች የተመደቡ አስተባባሪዎች ባቀረቧቸው መነሻ ሀሳቦች መሰረት ውይይት እንደተደረገባቸው ገልፀዋል። ከውይይቶቹ በመነሳት የታዩ ውስንነቶችን ለመቅረፍና አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ውይይት መሆኑን አቶ አሸናፊ አንስተዋል።
በዩኒቨርሲቲው ሴ/ህ/ወ/ጉ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አለሚቱ ብርሀኑ በምርምርና ጥናት የሚሳተፉ ሴት መምህራን ከወንዶች አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ነው ብለዋል። ስለሆነም ችግሩን ለማቃለል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ወ/ሮ አለሚቱ ገልፀዋል።
የ"NORHED ll ReRED" ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ ከበደ በአንፃሩ፤ በመጀመሪያው ዙር የታዩ ክፍተቶችን ለመገምገምና የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የሚመለከታቸው የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ በየኮሌጁ የተመደቡ ሴት መምህራን አስተባባሪዎች፣ የተቋሙ ሴት መምህራን እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን ገልጸውልናል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት